የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን ሴት ልጅ የስፖርት ዝግጅት ላይ ታየች
የፕሬዝዳንቱ ሴት ልጅ ወታደራዊ ባልሆነ ዝግጅት ላይ ስትታይ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው
በዝጅግቱ ላይ የታየችው የኪም ልጅ በቅርቡ ምስሏ በቴምብሮች ላይ የወጣው ኪም ጁ ኤ ልትሆን ትችላልች ተብሏል
የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን እና ሴት ልጃቸው የመንግስት ባለስልጣናት በተሳተፉበትን የስፖርት ዝግጅት መታየታቸው የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግቧል፡፡
የመንግስት ሚዲያዎቸ "ውድ ልጅ" እያሉ የሚጠሯት የፕሬዝዳንቱ ሴት ልጅ ወታደራዊ ባልሆነ ዝግጅት ላይ ስትታይ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው፡፡
የእግር ኳስ ውድድር በተካሄደበት የስፖርት ዝግጅቱ ላይ ስለተገኘችው ሴት ልጅ ስም በግልጽ የታወቀ ነገር ባይኖርም በቅርቡ ምስሏን በቴምብሮች ላይ የወጣው ኪም ጁ ኤ ልትሆን እንደምትችል እየተነገረ ነው፡፡
ኪም ጁ ኤ ቀጣይዋ የሰሜን ኮሪያ መሪ ልትሆን ትችላለች ተብላ የምትጠበቀው የፕሬዝዳንቱ ሴት ልጅ ናት፡፡
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኮሪያ ሴንትራል ቴሌቪዥንን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሚዲያዎች የፕሬዝዳንቱን ሴት ልጅን "ተወዳጅ" እና "የተከበረች" የመሳሰሉ ቅጽሎችን በማስቀደም የተለያዩ ዜናዎች የሚሰሩላትም ናት ኪም ጁ ኤ፡፡
“የኪም ወራሽ” የሚል ርዕስ ይዘው የወጡ መገናኛ ብዙሃም አሉ ፤ ምንም እንኳን ቀጣይዋ የፒዮንጊያንግ መሪ ናት የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ ቢሆንም፡፡
እንደ ደቡብ ኮሪያ ሚዲያዎች መረጃ ከሆነ በመገናኛ ብዙሃን እምብዛም ስሟ የማይታወቀው ፕሬዝዳንቱ ልጅ ፤ አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ኮከብ ዴኒስ ሮድማን በ2013 ፒዮንግያንግ ላይ ያገኛት የኪም ሁለተኛ ሴት ልጅ ሳትሆን አትቀርም፡፡
በተጨማሪም ከፍተኛ ስልጣን እንዳላቸው የሚነገርላቸው የሰሜን ኮሪያው መሪ እህት ኪም ዮ ጆንግ በዝግጅቱ ላይ ታይተዋል፡፡
የኮሪያ ሴንትራል ኒውስ ኤጄንሲ በለቀቀው ፎቶ ላይም ኪም ዮ ጆንግ ከኋለኛው ረድፍ ተቀምጠው ያሳያል፡፡
ዝግጅቱ የተካሄደው በሰሜን ኮሪያ ውስጥ ‘የአብረቅራቂ ኮከብ ቀን’ ተብሎ የሚጠራውን ታላቅ በዓል ለማክበር ነው።
‘የአብረቅራቂ ኮከብ ቀን’ የሀገሪቱ መስራች የሆኑትን የቀድሞው የሰሜን ኮሪያ መሪ ጄኔራል ኪም ጆንግ ኢል ልደት ለመዘከር ሰሜን ኮሪያውያን የካቲት ወር ላይ የሚያከብሩት በዓል ነው፡፡
የዝግጅቱ ተሳታፊዎች "ዘንድሮ በሪፐብሊኩ የልማት ጉዞ ላይ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ጠንከር ያለ ውሳኔ አሳልፈዋል "ም ነው የተባለው፡፡