ኪም ጁ ኤ በመባለ የምትታወቀው የፕሬዝዳንቱ ልጅ ቀጣይ “የኪም ወራሽ” ልትሆን እንደመትችል ይነገራል
ሰሜን ኮሪያ የኪም ጆንግ ኡን ሴት ልጅ የሆነችውን ኪም ጁ ኤ ምስል የሚያሳዩ አዳዲስ ቴምብሮች ይፋ ልታደርግ ነው፡፡
ቢዘህም መሰረት መቀመጫው በፒዮንግያንግ ላይ ያደረገው የኮሪያ ፖስታ ቤት ከሚያወጣቸው 11 ቴምብሮች ውስጥ በአምስቱ ውስጥ የኪም ሴት ልጅ ምስል እንደሚገኝ የመንግስት ኮርፖሬሽን ድረ-ገጽ ዘግቧል።
በተጨማሪም አዲሶቹ ቴምብሮች ኪም ጆንግ-ኡን የኒውክሌር መከላከል አቅምን ለማጠናከር በሚል ባለፈው አመት ህዳር 18 ላይ የ"ህዋሶንግ-17" አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳይልን ሲፈተሹ የሚያሳይ ምስል ያላቸው ናቸውም ተብሏል፡፡
አሁን ላይ ምስሏ በተለያዩ የሰሜን ኮሪያ ፖስታ ቤት ቴምብሮች ብቅ ያለው የፕሬዝዳንቱ ልጅ ኪም ጁ ኤ የአህጉር አቋራጭ ሚሳይል ሙከራ ከተደረገበት ከህዳር ወር ወዲህ ፤ በቅርቡ የሰሜን ኮሪያ ህዝባዊ ጦር የመስርታ በአል ላይ የነበረው ወታደራዊ ሰልፍን ጨምሮ ከኪም ጋር የታየችው አራት ጊዜያት ብቻ ነበር፡፡
በሰልፉ ላይ የኪም ጁ ኤ መታየት ምናልባትም ቀጣይዋ የሰሜን ኮሪያ መሪ ልትሆን ትችላለች የሚሉ ወሬዎች በስፋት እንዲሰራጩም ምክንያት ሆኖ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
በሌላ በኩል የኪም ሴት ልጅ በበአሉ የተገኘችው “የቤተሰብ አባል” ሆና ነው የሚሉም ነበሩ፡፡ ያም ሆኖ የሰሜን ኮሪያው መሪ ሴት ልጅ ኪም ጁ ኤ ምስል አሁን ላይ በቴምብሮች መምጣቱ የበርካቶች ቀልብ የሳበ ጉዳይ መሆኑ አልቀረም፡፡
አዲሶቹ ቴምብሮች ኪም ጁ ኤን "ውድ ልጅ" በማለት ይገልጿታል፡፡
የኮሪያ ሴንትራል ቴሌቪዥንን ጨምሮ ሌሎች በርካታ ሚዲያዎችም እንዲሁ የፕሬዝዳንቱን ሴት ልጅን "ተወዳጅ" እና "የተከበረች" የመሳሰሉ ቅጽሎችን በማስቀደም የተለያዩ ዜናዎች ሲያሰራጩ ተስተውለዋል፡፡
“የኪም ወራሽ” የሚል ርዕስ ይዘው የወጡ መገናኛ ብዙሃም አሉ፤ ምንም እንኳን ኪም ቀጣዩ መሪ አድርገው ሾሟታል የሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ አስቸጋሪ ቢሆንም፡፡
በመገናኛ ብዙሃን እምብዛም ስሟ የማይታወቀው ፕሬዝዳንቱ ልጅ ፤ አሜሪካዊው የቅርጫት ኳስ ኮከብ ዴኒስ ሮድማን በ2013 ፒዮንግያንግ ላይ ያገኛት የኪም ሁለተኛ ሴት ልጅ ሳትሆን እንደማትቀርም ነው የደቡብ ኮሪያ ሚዲያዎች መረጃ የሚያመለክተው፡፡