ፒዮንግያንግ፥ አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ ሊያደርጉ ያሰቡትን ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ካላስቀሩ “ከባድ እርምጃ” እወስዳለሁ ማለቷ ይታወሳል
ሰሜን ኮሪያ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ባለስቲክ ሚሳኤል ማስወንጨፏ ተነገረ።
ከአርባ ሰባት ቀናት በኋላ ያስወነጨፈችው ሚሳኤል በጃፓን ባህር ውስጥ መውደቁንም ነው የጃፓን ባለስልጣናት የገለጹት።
ፒዮንግያንግ ዛሬ ያስወነጨፈችው ባለስቲክ ሚሳኤል ባለፈው አርብ ለአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ የሰጠችው ማስጠንቀቂያ ምላሽ ተደርጎ ተወስዷል።
ዋሽንግተን እና ሴኡል የፊታችን ረቡዕ በፔንታጎን ሊያደርጉት ያሰቡት ውይይትና ይህን ተከትሎ የሚካሄድ ግዙፍ ወታደራዊ ልምምድ ፒዮንግያንግን አስቆጥቷል።
ሀገራቱ ጸብ አጫሪ ድርጊታቸውን የማያቆሙ ከሆነ “ከባድ ምላሽ” እንደምትሰጥ የዛቱት ኪም ጆንግ ኡን፥ ዛሬ ረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ ሚሳኤል አስወንጭፈዋል።
ከፒዮንግያንግ በቅርብ ርቀት በምትገኘው ሱናን አውሮፕላን ማረፊያ ላይ ተወነጨፈ ስለተባለው ሚሳኤል ሰሜን ኮሪያ ማረጋገጫ አልሰጠችም ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
ባለፈው አመት ከ70 በላይ የሚሳኤል ሙከራዎችን ያደረገችው ሰሜን ኮሪያ የአህጉር አቋራጭ ሚሳኤሎችን የሚመለከት ወታደራዊ ክንፍ ማቋቋሟ ተገልጿል።
በቅርቡ የሀገሪቱን ጦር 75ኛ አመት ስታከብር ለእይታ ያበቃቻቸው አዳዲስ ሚሳኤሎችም ፒዮንግያንግ ከፈረንጆቹ 2017 ወዲህ የመጀመሪያውን የኒዩክሌር የጦር መሳሪያ ለመሞከር መቃረቧን ያሳያል ተብሏል።
በደቡብ ኮሪያ ከ28 ሺህ በላይ ወታደሮች ያሏት አሜሪካም ይህን የሰሜን ኮሪያን “የአለም ሰላም ስጋትነት” ለመግታት በሚል ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር ትብብሯን አጠናክራለች።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ከሲኡል ጋር ልታደርገው ያሰበችው ወታደራዊ ልምምድም የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት እንዳያንረው ተሰግቷል።
ሰሜን ኮሪያ የባለስቲክ ሚሳኤልና የኒዩክሌር ፕሮግራሟ በመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ተደጋጋሚ ማዕቀቦች እንዲጣሉባት አድርጓል።
ፒዮንግያንግ ግን “የምዕራባውያኑን እና አጋሮቻቸውን ጸብ አጫሪ ድርጊት” መግቻው ብቸኛ መንገድ ይሄው ነው ብላ ቁጣዋን በሚሳኤል ማስወንጨፍ መግለጿን ቀጥላለች።