የሰሜን ኮሪያው መሪ እህት አሜሪካን በሚሳኤል አስጠነቀቁ
ፒዮንግያንግ በዛሬው እለት ሁለት ባለስቲክ ሚሳኤሎችን የሞከረች ሲሆን፥ አሜሪካ በፓስፊክ ቀጠና ያላትን ተጽዕኖ እንድትቀንስ አሳስባለች
ደቡብ ኮሪያና ጃፓንም የዛሬውን ሙከራ አጥበቀው ተቃውመው የጸጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርግ ጠይቀዋል
ሰሜን ኮሪያ ወደ ምስራቃዊ የባህር ዳርቻዋ ሁለት የባለስቲክ ሚሳኤሎችን ማስወንጨፏን አስታወቀች።
ሚሳኤሎቹ ከ390 ኪሎሜትር በላይ የሚምዘገዘጉ የአጭር ርቀት ሚሳኤሎች መሆናቸውንም ነው የሀገሪቱ ብሂራዊ የዜና ወኪል ኬ ሲ ኤን ኤ የዘገበው።
100 እና 50 ኪሎሜትር ከፍታ ላይ የተምዘገዘጉት ባለስቲክ ሚሳኤሎች ከጃፓን የውሃ ክልል ውጭ መውደቃቸውን የጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
- ሰሜን ኮሪያ የረጅም ርቀት ባለስቲክ ሚሳኤል አስወነጨፈች
- ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳይል ማስወንጨፏን ተከትሎ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የጋራ የአየር ልምምድ አደረጉ
የጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ፉሚዮ ኪሺዳ የጸጥታው ምክር ቤት በዛሬው እለት በፒዮንግያንግ ዙሪያ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርግ መጠየቃቸውንም ነው ሬውተርስ የዘገበው።
ደቡብ ኮሪያም የሚሳኤል ሙከራውን “ከባድ ጸብ አጫሪነት ነው” በሚል የተቃወመችው ሲሆን፥ በአራት የሰሜን ኮሪያውያን ላይ ማዕቀብ መጣሏን አስታውቃለች።
የፒዮንግያንን ተደጋጋሚ የሚሳኤል ሙከራ የአሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያን ወታደራዊ ትብብር ያጠናክረዋል፤ የሚጣሉ ማዕቀቦችንም ያበራክተዋል እንጂ መረጋጋት አያሰፈንም የሚል መግለጫንም የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር አውጥቷል።
የአሜሪካ ኢንዶ ፓስፊክ እዝ በበኩሉ የዛሬው የሚሳኤል ሙከራ ስጋት የሚፈጥር ባይሆንም፥ ሰሜን ኮሪያ የኒዩክሌር ፕሮግራሟን ቀጠናውን ለማተራመስ እየተጠቀመችበት መሆኑን ግን ያሳያል ብሏል።
የመንግስታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክም፥ ፒዮንግያንግ ከተጨማሪ ጸብ አጫሪ ድርጊት እንድትታቀብ እና ወደ ንግግር እንድትመለስ ጠይቀዋል።
የሰሜን ኮሪያው መሪ እህት ኪም ዮ ጆንግ በበኩላቸው፥ የአሜሪካ ወታደራዊ እንቅስቃሴ መጨመሩ የፓስፊክ ቀጠናን የጦርነት ማዕከል እያደረገው ነው ብለዋል።
ሀገራቸውም በአሜሪካ ተሳትፎ ልክ ፈጣን ምላሽ እንደምትሰጥ ነው ኪም ዮ ጆንግ ያሳሰቡት።
አሜሪካ በትናንትናው እለት ከደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ጋር በተናጠል ወታደራዊ ልምምድ ማድረግ መጀመሯን ተከትሎ ነው ፒዮንግያንግ ዛሬ ሚሳኤል ያስወነጨፈችው።
ከትናንት በስቲያም አህጉር አቋራጭ ሚሳኤል ያስወነጨፈችው ሰሜን ኮሪያ የፈረንጆቹ 2023 ከገባ ወዲህ ሶስተኛውን ሙከራ አድርጋለች።
ባለፈው አመት ከ70 በላይ የሚሳኤል ሙከራ ያደረገችው ሀገር፥ በዚህ አመትም ከጅምሩ የኮሪያ ልሳነ ምድርን ውጥረት የሚያንሩ እርምጃዎችን እየወሰደች ነው ተብሏል።
ኪም ዮ ጆንግ ግን ቀጠናውን እያመሱት ያሉት አሜሪካ እና አጋሮቿ ናቸው፤ ለማንኛውም እንቅስቃሴያቸውም ተገቢውን አጻፋ እንመልሳለን ሲሉ ዝተዋል።