የአለማችን ውዱ ሩዝ ከጣዕሙ ባሻገር በፋይበር እና ቫይታሚን ቢ1 ከመደበኛው ነጭ ሩዝ በብዙ እጥፍ ይልቃል ተብሏል
ሩዝ በአለማችን በርካቶች በተመጣጣኝ ዋጋ ይሸምቱታል የሚባልለት ምግብ ነው።
የተለየ ጣዕም እና መልክ ያለው ሩዝ ግን ከስጋ ዋጋ በእጅጉ ይልቃል።
በጃፓኑ “ቶዮ ራይስ ኮርፖሬሽን” የሚመረተው ሩዝ በአለም የድንቃድንቅ መዝገብ ሰፍሯል።
“ኪንሜማይ ፕሪሚየም” የሚል ስያሜ የተሰጠው ሩዝ አምስት በአለማቀፍ ደረጃ በጥራታቸው ሽልማት ያገኙ የሩዝ ዝርያዎችን በማጣመር የተፈጠረ ነው።
የሩዝ አምራቹ ኩባንያ ከ17 አመት በፊት ያስተዋወቀው ዘመናዊ ቴክኖሎጂ አምስቱን የሩዝ ዝርያዎች ልዩ ጣዕምና መልክ እንዲኖራቸው አድርጎ ለማዘጋጀት ስድስት ወራት ይፈጅበታል ተብሏል።
ከ180 ቀናት ሂደት በኋላ የሚገኘው “ኪንሜማይ ፕሪሚየም” በኪሎ 120 ዶላር (በዛሬው የንግድ ባንክ የውጭ ምንዛሬ ተመን ከ13 ሺህ 400 ብር በላይ) እንደሚያወጣም ነው ኦዲቲ ሴንትራል ያስነበበው።
የአለማችን ውዱ ሩዝ ሲፈለፈል የአልማዝ ፈርጥ ያላቸው የሚመስሉ ፍሬዎችን እንዲያወጣ መደረጉም ለሚወጣበት ወጪ የሚመጥን አስመስሎታል።
“ኪንሜማይ ፕሪሚየም” ከልዩ ጣዕሙ ባሻገር በፋይበር እና ቫይታሚን ቢ1 ከመደበኛው ሩዝ በብዙ እጥፍ ይልቃል ተብሏል።
ከተለመደው ነጩ ሩዝ 6 እጥፍ በሽታ የመከላከል አቅምን የሚያጎለብቱና ጤናን የሚጠብቁ ንጥረነገሮችን መያዙ የተገለጸ ሲሆን፥ የታጠበ እና ሲቀቀል ደስ የሚል ሽታ ያለው ስለመሆኑ ተነግሮለታል።
የአለማችን ውዱን ሩዝ የሚያመርተው የጃፓን ኩባንያ በጥራታቸው አለማቀፍ ሽልማት ያገኙ የሩዝ ዝርያዎችን ከአርሶ አደሮች ሲገዛ ከተለመደው ነጭ ሩዝ በሰባት እጥፍ ዋጋ ጨምሮ ይገዛል ነው የተባለው።
ይህም ዋጋውን አንሮት የአለም ድንቃድንቅ መዝገብ በ2016 የአለማችን ውዱ ሩዝ ብሎ እንዲመዘግበው አድርጎታል።
ሩዝ በብዛት በመጠቀም ከአለም ሀገራት ቻይና እና ህንድ ቀዳሚውን ደረጃ ሲይዙ ስምንተኛ ላይ ተቀምጣለች።