አሜሪካ ለሃይቲ የምትሸጠው ሩዝ ለካንሰር ሊያጋልጥ የሚችል ነው ተባለ
የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ባደረገው ጥናት ዋሽንግተን ለካሪቢያኗ ሀገር የምትልከው ሩዝ ለተለያዩ ህመሞች ተጋላጭነትን ከፍ የሚያደርግ መሆኑን አረጋግጧል
ሃይቲ ከ90 በመቶ የሩዝ ፍጆታዋን የምትሸፍነው ከአሜሪካ ሸምታ በማስገባት ነው
አሜሪካ ለሃይቲ የምትሸጠው ሩዝ ለካንሰር ሊያጋልጥ እንደሚችል ጥናት አመላከተ።
የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ ይፋ ያደረገው ጥናት አሜሪካ ለሃይቲ የምትልከው ሩዝ አርሰኒክ እና ካድሚየም የተሰኙ ማዕደናት ይዘቱ ከፍተኛ መሆኑን አረጋግጧል።
የእነዚህ ማዕድናት መጠን ከፍ ማለት ለካንሰርና ለልብ ህመም ተጋላጭነትን እንደሚጨምር ነው ጥናቱ የጠቆመው።
የካሪቢያኗ ሃይቲ በሀገር ውስጥ ከምታመርተው ሩዝ ይልቅ ከአሜሪካ የምታስገባው ዋጋው ርካሽ ነው፤ ይህም ከሜክሲኮ እና ጃፓን በመቀጠል የዋሽንግተንን ሩዝ በብዛት እንድታስገባ አድርጓታል።
ሀገሪቱ ከ90 በመቶ በላይ የሩዝ ፍጆታዋን ከአሜሪካ ገዝታ በምታስገባው ትሸፍናለች።
ሃይቲ ከአሜሪካ የምታስገባው ሩዝ አርሰኒክ እና ካድሚየም ይዘቱ በሀገር ቤት ከምታመርተው በእጥፍ የጨመረ መሆኑን የሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ በወሰድኩት ናሙና አረጋግጫለሁ ብሏል።
የማዕድናቱ ይዘት የአሜሪካ የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣን ካስቀመጠው ገደብ ከፍ ያለና በተለይ በህጻናት ጤና ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል መሆኑንም አመላክቷል።
ጥናቱ በተጀመረመት አመት (2020) ሃይቲያውያን በአመት በአማካይ 85 ኪሎግራም ሩዝ ይመገባሉ፤ ይህም ከአሜሪካ አማካይ (12 ኪሎግራም) በሰባት እጥፍ ይልቃል።
ዋሽንግተን በርካሽ የሩዝ ምርቷን ወደ ሃይቲ መላኳ የሃይቲ አርሶ አደሮችን ካለማበረታቱ ባሻገር ወጣቶችን ለተለያዩ የጤና እክሎች የመዳረግ እድሉ ከፍ ማለቱ አሳሳቢ ነው ብሏል ጥናቱ።
በመሆኑም ወደ ሃይቲ ሩዝ በሚልኩ የአሜሪካ ኩባንያዎች ላይ ምርመራ እንዲጀመርም ጠይቋል።
ጥናቱ አሜሪካ ለሌሎች ሀገራት የምትልከው የሩዝ ምርት ደህንነት ምን እንደሚመስል ግን ያለው ነገር የለም።
ለሚቺጋን ዩኒቨርሲቲ የጥናት ውጤት የምግብና መድሃኒት ቁጥጥር ባለስልጣንም ሆነ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ምላሽ መስጠት አልፈለጉም ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።