በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ክርክር ትራምፕ በባይደን ላይ የበላይነትን ተቀዳጅተዋል
ለ2024ቱ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩት ጆ ባይደን እና ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ምሽት የመጀመሪያውን የፊት ለፊት ክርክራቸውን አድርገዋል።
የረሲያ ዩክሬን ጦርነት ጉዳይን ጨምሮ ሌሎች ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮችን በቃኘው ክርክራቸው ላይ የሪፕሊካኑ ተወካይ ዶናልድ ትራምፕ የበላይነት የያዙበት ነው ተብሏል።
በክርክሩ ወቅትም ዶናልድ ትራምፕ “አሜሪካ ትክክለኛ እና በፑቲን የሚከበር ፕሬዝዳንት ቢኖራት ኖሮ ሩሲያ ዩክሬንን አትወርም ነበር” ሲሉ ተደምጠዋል።
ባይደን በበኩላቸው፤ “ቀጥል፣ ፑቲን ዩክሬንን ይቆጣጠር እና ከዚያ ወደ ፖላንድ እና ሌሎች ቦታዎች ይሸጋገር፤ ያኔ ምን እንደሚሆን ትመለከታለህ” ብለዋል። ትራምፕ ቀበል አደርገው “ስለ ምን እንደሚያወራ እንኳ አያውቅም” ሲሉ ባይደንን ወርፈዋል።
በባይደን እና ትራምፕ ክርክር ላይ ጥያቄ የቀረበላቸው የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቤተ መንግስት ክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሜትሪ ፔስኮቭ፤ ሩሲያ የአሜሪካን ምርጫ የአሜሪካ የውስጥ ጉዳይ እድርጋ ትመለከታለች ብለዋል።
ዲሜትሪ ፔስኮቭ፤ የፕሬዝዳንት ባይደን እና ዶናድ ትምፕን የመጀመሪያ ክርክር ባቀለለ ንግግራቸው፤ ክርክሩ ሩሲያ ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ አይደለም ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ክርክሩን ተመልክተው ይሆን? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄም፤ “ፕሬዚዳንት ፑቲን አላርም ሞልተው በሌሊት ከእንቅልፋቸው ተነስተው የአሜሪካን ክርክር ይመለከታሉ ማለት ዘበት ነው” ሲሉ መልስ ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጆ ባይደን እና በዶናልድ ትራምፕ መካከል የተደረገውን የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ክርክር ለመከታተል እኩለ ሌሊት ላይ ከእንቅልፋቸው አልተነሱም ሲሉም ተናግረዋል።
ዲሜትሪ ፔስኮቭ አክለውም፤ ሀገራችን ወሳኝ የሆኑ ብዙ ጠቃሚ ጉዳዮች አሉን፤ ፕሬዝዳንት ፑቲን እያስተናገዱ ያሉት እነዚህን ጉዳዮች ነው፤ በአሜሪካ የሚደረጉ ክርክሮች የእኛ ዋና ጉዳዮችን አይደለም ብለዋል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዚህ ቀደም፤ ከሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ይልቅ ዴሞክራቱን ጆ ባይደን እንደሚመርጡ መናገራቸው ይታወሳል።
ፕሬዝዳንቱ “ከባይደንና ከትራምፕ ለእኛ የተሻለው የቱ ነው?” የሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ ነው ያለምንም ማመንታት “የካበተ ልምድ ያለው ባይደን ይሻላል” የሚል ምላሽ የሰጡት።