ለ90 ደቂቃዎች የሚቆየውን ክርክር ሚሊየኖች በቀጥታ ስርጭት ይከታተሉታል ተብሎ ይጠበቃል
ባይደን እና ትራምፕ በዋይትሃውስ ለመቆየትና ወደ ነጩ ቤተመንግስት ዳግም ለመመለስ ዛሬ በቴሌቪዥን ክርክር ያደርጋሉ።
የ81 አመቱ የዴሞክራት እጩ ጆ ባይደን እና የ78 አመቱ ሪፐብሊካን ዶናልድ ትራምፕ በ2020 ሁለት ጊዜ የፊት ለፊት ክርክር አድርገዋል።
ከአራት ወራት በኋላ ለሚካሄደው ምርጫ የመራጮችን ቀልብ ለመያዝ ሁነኛ አጋጣሚን የሚፈጥረው የዛሬ ምሽቱ ግን ካለፉት ሁለት ክርክሮች የሚለዩት በርካታ ጉዳዮች አሉ።
ከእድሜያቸው መግፋት ጋር ተያይዞ በስብሰባ መሀል የሚያሸልቡት ባይደን ለ1 ስአት ከ30 በሚቆየው ክርክር የአዕምሮ ዝግጁነታቸው ይፈተሻል።
በቀረቡባቸው የወንጀል ክሶች ጥፋተኛ በመባል የመጀመሪያው የአሜሪካ (የቀድሞው) ፕሬዝዳንትነት የሆኑት ትራምፕም በ34ቱ ክሶች፣ የ2020ው ምርጫ ተጭበርብሯል በሚል በካፒቶል ሂል ላስነሱት አመጽና ሌሎች ጉዳዮች የሚሰጡት ምላሽም ተጠባቂ ነው።
ከአትላንታ የሲኤንኤን ስቱዲዮ በቀጥታ የሚካሄደውን ክርክር የዜና አንባቢዎቹ ጃክ ታፐር እና ዳና ባሽ ይመሩታል ተብሏል።
የኔልሰን ሚዲያ ተቋም ያወጣው ጥናት እንደሚያሳየው የ2020ውን የባይደንና ትራምፕ ክርክር 73 ሚሊየን ሰዎች በቀጥታ ተመልክተውታል።
የዛሬውን የ2024 ምርጫ የመጀመሪያ የእጩ ፕሬዝዳንቶች ክርክርም ሚሊየኖች እየተጠባበቁት ነው።