ከትራምፕ ይልቅ “ይበልጥ ተገማቹን” ባይደን እመርጣለሁ - ፑቲን
ፕሬዝዳንት ፑቲን ለባይደን የተሻለ ድጋፍ ቢሰጡም “የአሜሪካ ህዝብ ከሚተማመንበት ፕሬዝዳንት ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን” ብለዋል
ሩሲያ በ2016ቱ ምርጫ ትራምፕ ወደ ስልጣን እንዲመጡ ጣልቃ ለመግባት ሞክራለች በሚል ስትወቀስ ቆይታለች
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ይልቅ ዴሞክራቱን ጆ ባይደን እንደሚመርጡ ተናገሩ።
ፕሬዝዳንቱ ፓቨል ዛሩቢን ከተባለ ሩሲያዊ ጋዜጠኛ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ “ከባይደንና ከትራምፕ ለእኛ የተሻለው የቱ ነው?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል።
ፑቲን ያለምንም ማመንታት “የካበተ ልምድ ያለው ባይደን ይሻላል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
በጥቂቱ ፈገግ ብለውም “ነገር ግን የአሜሪካ ህዝብ ከሚተማመንበት የትኛውም ፕሬዝዳንት ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን” ሲሉ አክለዋል።
ፑቲን በ2024ቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ብርቱ ፉክክር ያደርጋሉ ተብለው በሚጠበቁት ባይደንና ትራምፕ ዙሪያ አስተያየት ሲሰጡ የትናንቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የዋሽንግተን እና ሞስኮ ግንኙነት በ60 አመት ውስጥ ዝቅተኛው ደረጃ ላይ ደርሷል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደንም አጋሮቻቸውን በማስተባበር ለኬቭ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በሞስኮ ላይ የተለያዩ ማዕቀቦች እንዲጣሉ ማድረጋቸው ይታወቃል።
በአንጻሩ ትራምፕ በዋይትሃውስ ቆይታቸው ፑቲንን ሲተቹ አልተደመጡም፤ በቅርቡም ሩሲያ ለኔቶ ተገቢውን መዋጮ የማያዋጡ አባል ሀገራትን እንድታጠቃ አበረታታለሁ ማለታቸው የሚታወስ ነው።
ፑቲን በትናንቱ ቃለምልልስ ድጋፋቸውን ያሳዩት ግን ለባይደን ነው።
በሀገራት ምርጫ ጉዳይ ጣልቃመግባት ስህተት ነው ያሉት የ71 አመቱ ፕሬዝዳንት፥ ከባይደን የአዕምሮ ጤና ጋር ተያይዞ ስለሚነሳው ጉዳይ ጥያቄ ቀርቦላቸውም ምላሽ ሰጥተዋል።
“ከባይደን ጋር ከሶስት አመት በፊት በስዊዘርላንድ ስንገናኝ የተለየ ችግር አልተመለከትኩባቸውም” ነው ያሉት።
የ81 አመቱ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት የመውደቅና ሌሎች ከእድሜያቸው ጋር በተያያዘ ለሚገጥማቸው ድንገተኛ ጉዳዮችም ፑቲን ተከላክለውላቸዋል።
ትራምፕንም “ የተገነባ ስርአትን መከተል የማይወድ ፖለቲከኛ ነው ይሉታል፤ አሜሪካ ከሌሎች ሀገራት ጋር ሊኖራት የሚገባውን ግንኙነት የሚመራበት የራሱ መንገድ አለው” ብለዋል።
ሩሲያ በ2016ቱ ምርጫ ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ዴሞክራቷን ሂላሪ ክሊንተን አሸንፈው ስልጣን እንዲይዙ ጣልቃ ለመግባት መሞከሯን የአሜሪካ ሴኔት የደህንነት ኮሚቴ ሪፖርት ማድረጉ አይዘነጋም።
ከ1999 ጀምሮ በጠቅላይ ሚኒስትርነት እና በፕሬዝዳንትነት በስልጣን ላይ ያሉትን ቭላድሚር ፑቲን፥ ባይደን በ10፤ ትራምፕ ደግሞ በስድስት አመት ይበልጧቸዋል።
በቀጣይ ወር የሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫም ተፎካካሪዎቻቸውን በጊዜ የቀነሱት ፑቲን ለአምስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን ማሸነፋቸው እንደማይቀር ይጠበቃል።