ክሬምሊን የአዘርባጃኑ አውሮፕላን በሚሳኤል ተመቷል በሚል የወጣውን ዘገባ ውድቅ አደረገ
የ38 ሰዎች ህይወት የተቀጠፈበት የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ መንስኤ እየተመረመረ ባለበት ወቅት የሩሲያን ስም ማንሳት እንደማይገባም አሳስቧል
ዩክሬን ከአዘርባጃን ወደ ሩሲያ ሲበር የነበረው አውሮፕላን በሩሲያ የአየር መቃወሚያ ሚሳኤል ተመቷል ማለቷ ይታወሳል
ክሬምሊን የአዘርባጃኑ አውሮፕላን በሚሳኤል ተመቷል በሚል የወጣውን ዘገባ ውድቅ አደረገ።
ኦስፔሪ የተሰኘው የአቪየሽን ደህንነት ተቋም "የቪዲዮ እና የአውሮፕላኑ ቁርጥራጭ ማስረጃዎች ምርመራ፣ በደቡብ ምዕራባዊ ሩሲያ የነበረው የአየር ደህንነት የአዘርባጃኑ አውሮፕላን በሩሲያ የአየር መቃወሚያ ሚሳኤል ተመቶ ሊሆን እንደሚችል ያመላክታሉ" ብሏል።
ወልስትሪት ጆርናል ይህንኑ ተቋም በመጥቀስም የ38 ሰዎች ህይወትን የቀጠፈው አደጋ ከሩሲያ ጋር ሊያያዝ እንደሚችል ዘግቧል።
የዩክሬን የተዛባ መረጃ ተከላከይ ተቋም ሃላፊ አንድሬይ ኮቫሌንኮም አውሮፕላኑ "በሩሲያ የአየር መቃወሚያ ጸረ ሚሳኤል ተመቷል" ማለታቸው ይታወሳል። ሃላፊው በአውሮፕላኑ ላይ የደረሰውን ጉዳት (ቀዳዳዎች) በምክንያትነት ጠቅሰዋል።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ግን አውሮፕላኑ የተከሰከሰበት ምክንያት እየተመረመረ ባለበት ወቅት የሩሲያን ስም ማጠልሸት ተገቢ አይደለም ብለዋል።
"የምርመራ ውጤቱ ሳያልቅ ግምት መግለጽ ስህተት ነው፤ እኛ (ሩሲያ) በፍጹም ይህን አናደርግም፤ ማንም እንዲህ አይነቱን ነገር አይፈጽምም" ሲሉም ነው ፔስኮቭ ለጋዜጠኞች የተናገሩት።
የአዘርባጃን አየርመንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን ከባኩ ወደ ሩሲያዋ ቺቺኒያ መዲና ግሮዥኒ በመብረር ላይ እያለ በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ምክንያት ወደ ኋላ ተመልሶ በካዛኪስታን አክታው ከተማ ለማረፍ ሲሞክር በእሳት ተያይዟል።
የአውሮፕላኑ መዳረሻ ግሮዥኒ ለዩክሬን ቅርበት ያላትና ኬቭ በተደጋጋሚ የሚሳኤል ጥቃት የፈጸመችባት ከተማ ናት። ሞስኮ ምናልባትም ከኬቭ የተተኮሰ ሚሳኤልን ለማክሸፍ የተጠቀመችው ጸረ ሚሳኤል አውሮፕላኑን ሳይመታው አልቀረም ቢባልም ክሬምሊን መረጃውን ውድቅ አድርጓል።
የአዘርባጃን ፕሬዝዳንት ኢልሃም አሊየቭም የአደጋው መንስኤ እየተመረመረ በመሆኑ አስቀድሞ የቢሆን ግምቶችን ከመስጠት መቆጠብ ይገባል ብለዋል።
አውሮፕላኑ የበረራ አቅጣጫውን የቀየረው በጭጋጋማ የአየር ሁኔታ ምክንያት መሆኑን በመጥቀስም አውሮፕላኑ በማረፍ ላይ እያለ አደጋው እንደገጠመው ተናግረዋል።
አዘርባጃን ዛሬ ሀሙስ ታህሳስ 17 ብሄራዊ የሀዘን ቀን እንዲሆን ማወጇ የሚታወስ ነው።