በአዘርባጃኑ አውሮፕላን መከስከስ አደጋ 38 ሰዎች መሞታቸው ተረጋገጠ
አውሮፕላኑ 62 መንገደኞችን እና አምስት የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ነበር
ፕሬዝደንቱ አሌይቭ የአደጋው መንሰኤ እንደማይታወቅ እና ሙሉ ምርመራ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል
በአዘርባጃኑ አውሮፕላን መከስከስ አደጋ 38 ሰዎች መሞታቸው ተረጋገጠ።
በካዛኪስታን አክታው ከተማ አቅራቢያ የተከሰከሰው አውሮፕላን ይዟቸው ሲበር ከነበሩት ተሳፋሪዎች ውስጥ 38 መሞታቸው ተገልጿል።
ንብረትነቱ የአዘርባጃን ኤየርላየንስ የሆነው አውሮፕላን ከባኩ ወደ ሩሲያዋ ራስ ግዛት ቺቺኒያ ዋና ከተማ ግሮዥኒ ለመድረስ እቅድ ይዞ የነበረ ቢሆንም አቅጣጫውን ቀይሮ ካዛኪስታን ውስጥ ተከስክሷል።
ከአደጋው የተረፉት 29 ሰዎች ሆስፒታል ውስጥ ገብተው ህክምና እየተደረገላቸው ነው።
የበራራ ቁጥሩ ጄ2-8243 የሆነው ኢምብራኤየር አውሮፕላን ከታቀደው መንገድ ውጭ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኪሎሜትሮችን በማቋረጥ ከካስፒያን ባህር ጠረፍ በተቃራኒ ተከስክሷል።
የሩሲያ የአቪየሺን ዎችዶግ ወይም በራራ ተከታታይ ቡድን አደጋው የተፈጠረው በወፍ ምክንያት እንደሆነ ቢገልጽም የአቪየሺን ባለሙያዎች ይህ የመሆን እድሉ አነስተኛ ነው ይላሉ።
ባለስልጣናት የአደጋውን መንስኤ ምን እንደሆነ ወዲያውኑ አልገለጹም። ነገርግን አደጋው የተከሰተው የዩክሬን ድሮኖች በዚህ ወር በደቡብ ሩሲያ የምትገኘውን የቺቺኒያ ግዛት ማጥቃቷ ከተገለጸ በኋላ ነው።
አውሮፕላኑ ከበረረበት መስመር በቅርብ ርቀት ያለ የሩሲያ ኤየርፖርት በትናንትናው እለት ጠዋት ተዘግቶ ነበር። ዩክሬን አውሮፕላኑ ሲያቀናባት የነበረችውን ግሮዥኒን በዚህ ወር ማጥቃቷን አልገለጸችም።
የአዘርባጃኑ ፕሬዝደንት ኢልሃም አሌይቭ በደረሳቸው መረጃ መሰረት አውሮፕላኑ መንገዱን የቀየረው በአስቸጋሪ የአየር ሁኔታ ምክንያት ነው ብለዋል። ነገርግን ፕሬዝደንቱ አክለውም የአደጋው መንሰኤ እንደማይታወቅ እና ሙሉ ምርመራ መደረግ እንዳለበት ተናግረዋል።
"ይህ የአዘርባጃን ህዝብ ከባድ ሀዘን ውስጥ እንዲገባ ያደረገ አሳዛኝ ክስተት ነው" ነው ብለዋል ፕሬዝደንቱ።
አውሮፕላኑ 62 መንገደኞችን እና አምስት የበረራ ሰራተኞችን አሳፍሮ ነበር።
የካዛኪስታን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ከአዘርባጃን ከመጡ የልኡክ ቡድን ጋር አደጋው በደረሰበት አክታው ስብሰባ ባደረጉበት ወቅት የሟቾችን ቁጥር ይፋ ማድረጋቸውን ሮይተርስ የሩሲያው ኢንተርፋክስ የዜና አገልግሎት ጠቅሶ ዘግቧል።
የካዛኪስታን የአደጋ ጊዜ ሚኒስቴር አውሮፕላኑ ከመሬት ጋር ሲጋጭ የተፈጠረውን እሳት ማጥፋቱን እና ሁለት ህጻናትን ጨምሮ በህይወት የተረፉ ሰዎችን ማንሳቱን ገልጿል።