የጸጥታው ምክር ቤት በሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራ ዙሪያ “ዝምታን መምረጡ” አሳፋሪ ነው - አሜሪካ
የሰሜን ኮሪያን የሰሞኑ የሚሳይል ሙከራ ተከትሎ የጸጥታው ምክር ቤት ለአስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጧል
ሩሲያ፤ "ፒዮንግያንግን ለመተቸት ስብሰባዎችን ማብዛት ተገቢ አይደለም" ብላለች
በሰሜን ኮሪያ የወቅቱ የሚሳይል ሙከራ ጉዳይ የጸጥታው ምክር ቤት “ምንም አለማለቱ” እሜሪካን ማስቆጣቱ ተገለጸ፡፡
በተባበሩት መንግስታት የአሜሪካ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ በሰሜን ኮሪያ ጉዳይ ለመምከር በተጠራው አስቸኳይ የምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር ምክር ቤቱ “እርምጃ የለሽ ነው” ሲሉ ወቅሰዋል፡፡
“ሰሜን ኮሪያ ተደጋጋሚ በደል ብታደርስም ሁለት ቋሚ አባላት ዝም እንድንል አስገድደውናል” ሲሉም ተናግረዋል አምባሳደሯ፡፡
- የሰሜን ኮሪያው መሪ እህት አሜሪካን በሚሳኤል አስጠነቀቁ
- ሰሜን ኮሪያ አህጉር አቋራጭ ባላስቲክ ሚሳይል ማስወንጨፏን ተከትሎ አሜሪካና ደቡብ ኮሪያ የጋራ የአየር ልምምድ አደረጉ
አምባሳደሯ ሁለቱ ቋሚ አባላት ያሏቸውን ሀገራት በስም ባይጠቅሱም፤ ንግግራቸው በሰሜን ኮሪያ ላይ የሚጣለውን ማዕቀብ በመቃወም የሚታወቁት ሩሲያ እና ቻይና ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ ይገመታል፡፡
በዚህ ወሳኝ ጉዳይ ላይ ዝምታ መምረጥ ወደ ውድቀት ይወስደናል ያሉት ግሪንፊልድ፥ "የምክር ቤቱ ምንም እንቅስቃሴ አለማድረግ አሳፋሪ እና አደገኛ ነው" ሲሉም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡
እርምጃ አለመወሰዱ ሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራዎችን አጠናክራ እንድትቀጥል የሚያበረታታ መሆኑንም ጭምር በመግለጽ፡፡
በሰሜን ኮሪያ የሚወሰደውን እርምጃ የሚቃወሙ ሀገራትም ቢሆኑ እስያን እና ዓለምን አደጋ ላይ እየጣሉ መሆናቸውን ሊረዱ ይገባል ሲሉ አስጠቅቀዋል አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድ፡፡
እንደፈረንጆቹ በ 2017 ምክር ቤቱ ያጸደቀው ማዕቀብ ፒዮንግያንግን ለ5 ዓመታት ያልህ ከማንኛውም ትብኮሳ እንድትቆጠብ ያስገደደ እንደነበር የሚታወቅ ነው፡፡
አምባሳደር ግሪንፊልድ እንዳሉት ሩሲያ እና ቻይና ምክር ቤቱን ተልዕኮውን እንዳይወጣ መቃወማቸውን ከቀጠሉ ሰሜን ኮሪያ እነዚህን መሳሪያዎች የማበልጸግና ሙከራዎች የማድረግ ተግባራቶቿን የምትቀጥል ይሆናል፡፡
ሰሜን ኮሪያን ማስቆም አለብን ያሉት አምባሳደሯ፤ የጸጥታው ምር ቤት የሰሜን ኮሪያ እንቅስቃሴዎች የሚያወግዝ መግለጫ እንዲያወጣም ጠይቀዋል፡፡
ሰሜን ኮሪያ ባለፉት ቀናት ያካሄደችውን የሚሳይል ሙከራ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ጃፓን እንዲሁም ደቡብ ኮሪያን ጨምሮ 10 የጸጥታው ምክር ቤት አባላት አውግዘውታል፡፡
ሀገራቱ በጋራ ባወጡት መግለጫ "ሁሉም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አባል ሀገራት የሰሜን ኮሪያን ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት በማውገዝ ከእኛ ጋር እንዲተባበሩ እንጠይቃለን" ብለዋል፡፡
የጃፓኑ አምባሳደር ኢሺካኒ ኪሚሂሮ "ቀጣይ ትንኮሳዎችን በመፍራት የምንከተለውን ዝምታን የመምረጥ አካሄድ፤ ህጎቹን የሚጥሱ ሰዎች የጨዋታውን ህግ እንደፈለጉ እንዲጽፉ የሚያበረታታ ነው" ሲሉ ተናግረዋል፡፡
"አሁን ያለው መባባስ አደገኛ ነው፤ እናም ልንጋፈጠው ይገባል” ያሉት ደግሞ የፈረንሳዩ አምባሳደር ኒኮላስ ዴ ሪቪዬር ናቸው፡፡
አምባሳደሩ፤ “ ምክር ቤቱ ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ግዛት ሆናለች ብሎ ይቀበላል?" ሲሉም ጠይቀዋል፡፡
የሰሜን ኮሪያ እና የምዕራባውያን ፍጥጫ በተለይም የኮሪያ ልሳነ ምድርን ወደለየለት ቀውስ እንዳይወስደው ተሰግቷል፡፡
አሜሪካ እና አጋሮቿ የፒዮንጊያንግን ድርጊት ተንኳሽ ነው በሚል ቢያወግዙትም ሩሲያ እና ቻይና አሁንም ከፕሬዝዳንት ኪም ጆንግ ኡን ጋር የቆሙ ይመስላሉ፡፡
ሞስኮ እና ቤጂንግ እንደሚሉት ከሆነ አሁን በቀጠናው ለተፈጠረው ውጥረት ዋና ምክንያት አሜሪካ እና ደቡብ ኮሪያ እያደረጉት ያለው “የጋራ ወታደራዊ ልምምድ” ነው፡፡
በተመድ የሩስያ ምክትል ተወካይ ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ ያነሱትም "ዋሽንግተን እና አጋሮቹ በዚህ ጉዳይ ላይ ልዩ ኃላፊነት አለባቸው" የሚል ነው፡፡
"ፒዮንግያንግን ለመተቸት ስብሰባዎችን ማብዛት ተገቢ አይደለም" ም ነው ያሉት ዲሚትሪ ፖሊያንስኪ ፡፡