ሩሲያ “አውሬው-2” የተሰኘ አህጉር አቋራጭ ሚሳይል ልታስወነጭፍ ነው ተባለ
ምዕራባውያን ሞስኮ የተፈራውን ሚሳይል ልታስወነጭፍ ትችላለች በሚል ተጨንቀዋል
የፎረይን ፖሊሲ መጽሄት ሩሲያ በዩክሬን ላይ "አዲስ የጥቃት ማዕበል" ልትከፍት ትችላለች ሲል ዘግቧል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የሚሳይሎች ሁሉ ንጉስ እንደሆነ የሚነገርለትን ሃይፐርሶኒክ "አውሬው- 2" ወይም “ሳርማት” ሊያስወነጭፉ ይችላሉ በሚል ምዕራባውያን በከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ መሆናቸው ተገልጿል፡፡
እንደ እንግሊዙ "ዘ ኢንዲፔንደንት" ጋዜጣ ዘገባ ከሆነ ፑቲን በዩክሬን ላይ ዘመቻ የጀመሩበትን አንደኛ አመት ምክንያት በማድረግ 208 ቶን የሚመዝነውን "አውሬው- 2" ሚሳይል በቀናት ውስጥ በማስወንጨፍ ምዕራባውያንን ለማስደንገጥ ተዘጋጅተዋል፡፡
15 የኒውክሌር አረሮችን መሸከም የሚችለው ሚሳይል እንደፈረንጆቹ ከየካቲት 15 እስከ 25 ባለው ጊዜ ውስጥ ሊተኮስ እንደሚችልም ወታደራዊ ባለሙያዎች ለጋዜጣው ተናግረዋል።
የሚሳይሉን ሙከራ ለማድረግ በሩሲያ ሩቅ ምስራቅ ካምቻትካ አከባቢ ርቀው የሚገኙ ባለስልጣናት በዝግጅት ላይ መሆናቸውም ነው የተገለጸው፡፡
በተጨማሪም አህጉር አቋራጭ የባላስቲክ ሚሳኤል ሙከራ በሰሜን ካምቻትካ በምስራቅ ሩሲያ ውስጥ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል።
ሚሳይሉን ከማስወንጨፍ በተጨማሪ ሩሲያ በ10 ቀናት ውስጥ በዩክሬን ላይ አዲስ ጥቃት ለመፈጸም 1800 ታንኮች፣ 700 አውሮፕላኖች ፣ 2700 መድፎች ፣ 810 የሮኬት ማስወንጨፊያዎችን እና 500ሺህ ወታደሯቸዋን ዝግጁ ማድረጓ ሮይተርስ አንድ የዩክሬን ባለስልጣንን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡
የፎረይን ፖሊሲ መጽሄት እንደዘገበውም ሩሲያ በዩክሬን ላይ "አዲስ የጥቃት ማዕበል" ልትከፍት ነው፡፡
የአሁን ወታደራዊ ዘመቻ ጦርነቱ ሲጀመር ከነበረበት መልክ የበለጠና የተጠናከረ እንደሚሆንም ነው የተገለጸው፡፡
“ሳርማት” ሚሳይል የሩሲያው ፕሬዝዳንት "ሮኬት ኪንግ" እያሉ የሚያወዱሱት እንዲሁም የሰሜን አትልንቲክ የጦር ቃል ኪዳን /ኔቶ/ “አውሬው -2” ብሎ የሚጠራው አህጉር አቋራጭ ሚሳይል ነው፡፡
ሚሳይሉ 15 የኒውክሌር አረሮች የሚሸከም፣ 116 ጫማ ርዝመት ያለው እንዲሁም ከ1600 ማይል ርቀት በስድስት ደቂቃ ውስጥ ወደ ብሪታንያ መድረስ የሚችል መሆኑም ይነገራል።
የሩስያ ፕሬዝደንት ፑቲን አህጉር አቋራጭ ባሊስቲክ ሚሳይሉ በሰሜን ወይም በደቡብ ዋልታ ላይ መብረር በመቻሉ እና በዓለም ላይ ማንኛውንም ኢላማ የመመታ በመሆኑ በከፍተኛ ኩራት ማወደሳቸው ይታወሳል፡፡
"ምንም አይነት የመከላከያ ስርዓቶች ሊቋቋሙት አይችሉም፤ “ሩሲያን ለመፈታተን የሚፈልጉ ጠላቶቻችን ቆም ብለው ሁለት ጊዜ እንዲያስቡ እናደርጋለን" ሲሉም ነበር የተናገሩት ፑቲን የሚሳይኩን ሙከራ በተደረገበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፡፡