የአልበሽር ለአይ.ሲ.ሲ ተላልፎ መሰጠት ጉዳይ “በሱዳን ካቢኔ አባላት መካከል መከፋፈልን ፈጥሯል” ተባለ
መርያም ሱዳናውያን አብዮታቸውን የሚቀለብስ ማንኛውም አይነት የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አይፈቅዱምም ብለዋል
የመፈንቅለ መንግስት ሙከራው የክፍፍሉ ነጸብራቅ ነውም ብለዋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ
የቀድሞውን ፕሬዝዳንት አል በሽርን ለዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (አይ.ሲ.ሲ) አሳልፎ የመስጠቱ ጉዳይ በሱዳን ካቢኔ አባላት መካከል መከፋፈል እንደፈጠረ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መርያም አል ሳዲቅ አል ማህዲ ተናገሩ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሲቪል እና ወታደራዊ አመራሮችን ባካተተው ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ውስጥ መከፋፈል ተፈጥሯል ብለዋል፡፡
የሱዳን መፈንቅለ መንግስት ሙከራን ተከትሎ የሲቪልና ወታደራዊ አመራሮች እየተካሰሱ ነው
“የአልበሽር ጉዳይ በዘ-ሄግ ወይስ በካርቱም በሚቋቋምና በአይ.ሲሰ.ሲ በሚመራ የፍርድ ሂደት ይዳኝ” የሚሉ ውይይቶች እንደነበሩ ያስታወሱት ሚኒስትሯ የጋራ ስምምነት ላይ መድረስ እንዳልተቻለም ተናግረዋል፡፡
“የሽግግር ምክር ቤቱ በአል በሽር ብቻም ሳይሆን ግልጽ እንዲሆኑለት የሚጠይቃቸው የተለያዩ ጉዳዮች አሉ፤ በእኛ በሲቪል አመራሮቹ በኩል ደግሞ አልበሽርም ሆነ ሌሎች የሰብዓዊ ጉዳዮች ሚኒስትር የነበሩትን አህመድ ሃሮን መሰል የቀድሞ ተጠርጣሪ ሚኒስትሮች ለአይ.ሲ.ሲ ይቅረቡ የሚል ግልጽ አቋም ነበረን”ም ነው ሚኒስትሯ ያሉት፡፡
ለእኛ “አልበሽርን አሳልፎ ለመስጠት ብቻም ሳይሆን የዳርፉር ሰለባዎች ፍትህ እንዲያገኙ ለማድረግ ቁርጠኝነቱ አለን፡፡ ሆኖምም አይ.ሲሲ በአልበሽር አገዛዝ የተፈጸሙትን ወንጀሎች ሰፋ አድርጎ እንዲመረምር እና የፍርድ ሂደቱን ከ2002-2004 ባለው ጊዜ ብቻ እንዳይገድብ እንፈልጋለን። እንደ አለመታደል ሆኖም በምክር ቤቱ አባላት መካከል ይህን ጨምሮ ሌሎች ውሳኔዎች እንዴት ይተገብሩ በሚለው ላይ መኳኋን የለም”ም ብለዋል፡፡
“የግልበጣ ሙከራው በጦር ኃይሉ የውስጥ እና የውጭ አካላት የተቀናበረ ነው”- ጠ/ሚ አብደላ ሃምዶክ
በቅርቡ በሱዳን የተደረገውን ያልተሳካ መፈንቅለ መንግስት የተካሄደው በቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር አል-በሽር ታማኝ ወታደራዊ መኮንኖች ነው ከመባሉ ጋር ተያይዞ አስታየታቸውን የሰጡት መርየም ሙከራው “በሱዳን ውስጥ ብልጭ ያለውን እውነተኛ ዲሞክራሲ የሚያጨልም ነው” ብለዋል፡፡
ሚኒስትሯ ድርጊቱ በሱዳናውያን እንዲሁም በወታደራዊ መዋቅሩ መካከል መከፋፈሎች እንዳሉ ማመላከቱን ግን አልሸሸጉም፡፡
ሱዳን ነጻነቷን ከተቀዳጀችበት እንደፈረንጆቹ ከ1956 ወዲህ ተደጋጋሚ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራዎችን አስተናግዳለች፡፡
የራሳቸው የመርየም አባት፤ ሳዲቅ አል መህዲ በ1989 የሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ከተመረጡ በኋላ ነበር አል በሽር በመሩት ግልበጣ ከስልጣን የተወገዱት፡፡
ሆኖም ሱዳን አሁን በእንዲህ ዐይነቱ ሁኔታ የምትሸነፍ እንዳልሆነች ገልጸዋል፡፡
“ሱዳናውያን አብዮታቸውን የሚቀለብስ የትኛውንም ዐይነት የግልበጣ ሙከራ አይፈቅዱም”ም ነው መርየም ያሉት፡፡
ምስራቅ ሱዳን ተገቢውን ፖለቲካዊ ውክልና እና ጥቅም የማያገኝ ከሆነ ራሱን የቻለ ሀገር ይሆናል- የቤጃ ጎሳ መሪ
ለ30 ዓመታት ይዘውት ከቆዩት ስልጣን የተወገዱትና አሁን በእስር ላይ የሚገኙት አል በሽር በሙስና እና በሌሎችም ክሶች በሃገራቸው የሚፈለጉ ቢሆንም በአገዛዛቸው ተፈጽመዋል በሚባሉ ጅምላ ጭፍጨፋዎች፣ በጦር እና በሰብዓዊነት ላይ በተቃጡ ወንጀሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ይፈለጋሉ፡፡
ከ300 ሺ በላይ ሰዎች ባለቁበት የዳርፉር ግጭት 2 ነጥብ 5 ሚሊዬን ሰዎች መፈናቀላቸውን ከዘ ናሽናል የተገኘው ዘገባ አመልክቷል፡፡