ሩሲያ 45 የዩክሬን ድሮኖችን መትታ መጣሏን አስታወቀች
ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ጦርነት ከጀመረች ወዲህ በሞስኮ ዙሪያ ከፍተኛውን የድሮን ጥቃት ሙከራ ማድረጓ ተገልጿል
በሩሲያ ምዕራባዊ ክፍል ድንበር ጥሶ ከገባው የዩክሬን ጦር ጋር ውጊያው ቀጥሏል
የሩሲያ መዲና ሞስኮ ከዩክሬን የተቃጣባትን የድሮን ጥቃት ስታከሽም ማምሸቷን ገለጸች።
ኬቭ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረበት የካቲት 2022 ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ድሮኖች ወደ ሞስኮ ክልል በመላክ ጥቃት ለማድረስ መሞከሯን የሩሲያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ትናንት ምሽትም በሞስኮ ከተማ አቅራቢያ 11 ድሮኖች በአየር መቃወሚያዎች ተመተው መውደቃቸውን ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው።
ከኩርስክ ክልል ጋር በሚዋሰነው ቤርያንስክ 23:፥ በቤልጎሮድ 6፣ በካሉጋ ክልል ሶስት እንዲሁም በኩርስክ 2 ድሮኖች በድምሩ 45 ድሮኖች ጥቃት ሳያደርሱ ተመተው መውደቃቸውን የሩሲያው አርአይኤ ዘግቧል።
የድሮን ጥቃቱ መዲናዋን ሞስኮ ጨምሮ በፕሬዝዳንት ፑቲን የትውልድ ከተማ ሴንት ፒተርስበርግ እንዲሁም በምዕራባዊ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ኢላማ ያደረገ ነበር ተብሏል።
ክሬምሊን በምዕራባዊ ሩሲያ ዘልቃ በመግባት ጥቃት ማድረሷን የቀጠለችው ዩክሬን ባለፉት 24 ስአታት ለማድረስ የሞከረችው የድሮን ጥቃት መጠን ከእስካሁኖቹ በእጅጉ የላቀ መሆኑን ገልጿል።
ይሁን እንጂ ተመተው የወደቁት ድሮኖች ስላደረሱት ጉዳት እስካሁን ማብራሪያ አልሰጠም ብሏል ሬውተርስ በዘገባው።
የሩሲያ መገናኛ ብዙሃን የዩክሬን ድሮኖች በሞስኮ ክልል ተመተው ሲወድቁ የሚያሳዩ ምስሎችን እያጋሩ ነው።
የዩክሬን ጦር በበኩሉ ትናንት ምሽት በሮስቶቭ ክልል የሚገኘውን የሩሲያ ኤስ-300 የአውሮፕላን መቃወሚያ ስርአት ማውደሙን ገልጿል።
የዩክሬን ጦር በሩሲያ “ዘመቻ” ከጀመረ ዛሬ 17ኛ ቀኑን የያዘ ሲሆን፥ እስካሁን በፈጸመው ጥቃት በጥቂቱ የ31 ሩሲያውያን ህይወት ማለፉንና ከ140 በላይ መቁሰላቸውን የሩሲያው ታስ አስነብቧል።
ኬቭ የሩሲያን ድንበር ጥሳ ጥቃት ማድረስ የጀመረችው ሞስኮን አስገድዳ ወደ ድርድር ጠረጼዛ ለማምጣት በማለም እንደሆነ ቢነገርም ከባድ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል ተገምቷል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛካሮቫም “ዩክሬን በከርስክ ክልል የጀመረችው ጥቃት ምንም አይነት የሰላም ድርድር እንዳይኖር አድርጓል” ብለዋል።
ሩሲያ ከ200 ሺ በላይ ዜጎቿን ለማፈናቀል ያስገደደውን የዩክሬን ጦር ከግዛቷ ለማስወጣት ብርቱ ትግል እያደረገች መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ በዩክሬን ተጨማሪ ይዞታዎችን በእጇ እያስገባችም ነው ተብሏል።