ህንድ ዩክሬን እና ሩሲያን ለማቀራረብ ጥረት እንደምታደርግ አስታወቀች
ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ በተፋላሚ ሀገራቱ መካከል ግንኙነት እንዲጀመር ጥረት እንደሚያደርጉ ተነግሯል
በመጪው አርብ ወደ ዩክሬን የሚያቀኑት ሞዲ ሀገራቱን ከማቀራረብ ባለፈ የማደራደር ሚና እንዲኖራቸው እንደማይፈልጉ ተገልጿል
የህንዱ ጠቅላይ ሚንስትር ናሪንድራ ሞዲ ሩሲያ እና ዩክሬንን ለማቀራረብ ጥረት እንደሚያደርጉ ተገለጸ፡፡
ሀገራቱ መልዕክት እንዲለዋወጡ እና ወደ መቀራረብ እንዲመጡ የራሳቸውን ሚና እንደሚወጡ ያስታወቁት ሞዲ ኬቭ እና ሞስኮን የማደራደር ሀላፊነት እንዲኖራቸው እንደማይፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ በመጪው አርብ ወደ ፖለንድ እና ዩክሬን የሚያቀኑ ሲሆን በእዚያም የቀጠናዊ እና የደህንነት ጉዳዮች ላይ ከሀገራቱ መሪዎች ጋር እንደሚመክሩ ይጠበቃል፡፡
የሶቭየት ህብረት መፈራረስን ተከትሎ ዩክሬን እንደ ነጻ ሀገር ከተመሰረተች ከሶስት አስርተ አመታት ወዲህ የህንድ ጠቅላይ ሚንስትር ዩክሬንን ሲጎበኝ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡
ጠቅላይ ሚንስትሩ ለአዲስ የስልጣን ዘመን በድጋሚ ከተመረጡ በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ባደረጉት ጉብኝት ወደ ሩሲያ አቅንተው ከፕሬዝዳነት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በነበራቸው ቆይታ ጦርነቱ ሊቆም በሚችልበት ሁኔታ ላይ ከፕሬዝዳንቱ የቀረበላቸው ማብራርያ ተስፋ እንደሰጣቸው ተናግረዋል፡፡
ሞዲ በዩክሬን በሚገኝው በደህንነት ስጋት ለሰአታት ብቻ በሚኖራቸው ቆይታ ከፕሬዝዳንት ቮለደሚር ዘለንስኪ ጋር በዚሁ የፑቲን ሀሳብ ዙርያ እንደሚነጋገሩ ይጠበቃል፡፡
ህንድ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት በዲፕሎማሲ እና ውይይት እንዲፈታ በተደጋጋሚ ጥሪ ከሚያቀርቡ ሀገራት መካከል ቀዳሚዋ ናት፡፡
ዘለንስኪ ግሎባል ሳውዝ በመባል የሚታወቀውን ህንድ የምትገኝበትን ቀጠና ድጋፍ ለማግኝት ህንድን መወዳጀት ወሳኝ እንደሆነ ይገነዘባሉ፡፡
በዚህም ዩክሬን በሲውዘርላንድ ባደረገቻቸው የሰላም ጉባኤዎች ላይ ኒውደልሂ እንድትሳተፍ ተደጋጋሚ ጥሪዎችን አቅርባለች፡፡
የዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ሁለቱን ሀገራት ለማቀራረብ እና ለማስማማት ማንኛውም ባለብዙወገን ድርጅት እና ሀያላን ሀገራት ሁነኛ ጥረት ሲያደርጉ አልተስተዋሉም፡
ሞዲ ይህን ጦርነት ለመቋጨት ዲፕሎማሲ ዋነኛው መንገድ እንደሆነ ቢያምኑም በአደራዳሪነት ለመወከል ፈቃደኛ ስላልሆኑበት ምክንያት ግን የተባለ ነገር የለም፡፡