መንግስት ለህወሓት ከፍተኛ አመራሮች “የመጨረሻ” የእጅ ስጡ ጥሪ አቀረበ
መግለጫው ዜጎች ያለ ሥጋት ወደ ቀደመው ኑሯቸው እንዲመለሱ መመሪያ ተላልፏል ተብሏል
መንግስት በመግለጫው የህወሓት አመራሮች እጃቸውን መስጠት “…ተጨማሪ ሀገራዊ ኪሣራ እንዳይደርስ እና በከንቱ የዜጎች ደም እንዳይፈስ“ያደርጋል ብሏል
በወንጀል ድርጊት ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ፣ የፍርድ ቤት የመያዣ ትእዛዝ የወጣባቸው ከፍተኛ የህወሓት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች፣በድጋሚ እጃቸውን እንዲሰጡ መንግስት ጥሪ አቀረበ፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት “ከሕገ ወጡ የሕወሐት ቡድን ጋር ለተባበሩ አካላት ከመንግሥት የተሰጠ የመጨረሻ ማሳሰቢያ” በሚል ርዕስ ባወጣው መግለጫ ላይ የህወሃት ከፍተኛ የፖለቲካና ወታደራዊ አመራሮች ለሕግ አስከባሪ ተቋማት በሰላም እጅ እንዲሰጡ ጥሪ መቅረቡን ይገልጻል፡፡
“አመራሮቹ ይህንን ማድረጋቸው እስከዛሬ ከደረሰው ሀገራዊ ጥፋት እና ጉዳት በመማር፣ ለፍትሕ ራሳቸውን በማቅረብ፣ ተጨማሪ ሀገራዊ ኪሣራ እንዳይደርስ እና በከንቱ የዜጎች ደም እንዳይፈስ“ ያደርጋል ያለው መግለጫው ይሄንን የሚያደርጉ ከፍተኛ የሕወሐት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች “ራሳቸውን ከከፋ ቅጣት፣ ወገናቸውን ከመጎሳቆል ይታደጉታል“ ብሏል፡፡
መንግስት ያቀረበውን ይህ የእጅ ስጡ ጥሪ የመጨረሻ መሆኑንም መንግስት በመግለጫው ላይ አካቷል፡፡ ይንን በማያደርጉ የህወሃት ከፍተኛ ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ ሕግ የሚፈቅደውን አስፈላጊውን ሁሉ እንደሚደረግም መንግስት አስታውቋል፡፡
በመግለጫው በወንጀል ተግባራት ጉልህ ተሳትፎ እንዳላቸው ከተጠረጠሩ እና በዚህም ምክንያት የፍርድ ቤት መያዣ ከወጣባቸው ከፍተኛ የሕወኃት ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ አመራሮች በስተቀር ሌሎች ዜጎች ያለ ሥጋት ወደ ቀደመው ሰላማዊ ኑሯቸው እንዲመለሱም መንግስት ጥሪ አስተላልፏል፡፡ እነዚህ ዜጎች በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ ቀያቸው እና መኖሪያቸው በመመለስ ቀደመ ኑሯቸውን እንዲመሩም ነው ጥሪው የቀረበው፡፡
ወደ ሰላማዊ ኑሯቸው የሚመለሱ የክልሉ ተወላጅ ዜጎች፣ የትኛውም የሕግ ተጠያቂነት ሳይኖርባቸው፣ ከጥፋት ተቆጥበው፣ ወደ ሥራቸው እና ኑሯቸው በሰላም መሠማራት እንደሚችሉም መግለጫው አስታውቋል፡፡ ይህንን ለማድረግም ለሚመለከታቸው የጸጥታ፣ የአስተዳደር እና የሕግ አስከባሪ ተቋማት መመሪያ መተላለፉን ጽ/ቤቱ አስታውቋል።