ጠ/ሚ ዐብይ የህወሓት ቡድን ወደ ህግ መቅረብ እንዳለበት ለህብረቱ ልኡካን በአጽንኦት ገለጹ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ መከላከያ በትግራይ የመጨረሻ የህግ ማስከበር ዘመቻ እንዲያካሂድ አዘዋል
የፌደራል መንግስት የህወሓትን ጠብአጫሪነት መታገሱንና በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ሲያደርስ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን ለልኡኩ ተናግረዋል
የፌደራል መንግስት የህወሓትን ጠብአጫሪነት መታገሱንና በሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ሲያደርስ እርምጃ ለመውሰድ መገደዱን ለልኡኩ ተናግረዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የህወሓት ቡድንና በማይካድራ ዘግናኝ የሰብአዊ መብት ጥሰት የፈጸሙ ግለሰቦች ወደ ህግ ፊት መቅረብ እንዳለባቸው ለአፍሪካ ህብረት ልኡካን በአጽንኦት መናገራቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ግጭት ጉዳይ የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርና የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎዛ የቀድሞ የላይቤሪያ ፕሬዘዳንት ኢለን ጆንሰን ሰርሊፍን፣የቀድሞ የሞዛምቢክ ፕሬዘዳንት ጃኪይም ቺዛኖንና የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዘዳንት ክጋሌማ ሞትላንቴን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚልኩ አስታውቀው ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይም የህብረቱን ልኡክ አባላትን በዛሬው እለት ማግኘታቸውንና በትግራይ እየተካሄደ ስላለው የህግ ማስከበር ዘመቻ ምን እንደሚመስል ማስረዳታቸውን ጽ/ቤቱ ያወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
መንግስት የህወሓትን ጠብ አጫሪነት ለረጅም ጊዜ መታገሱን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በመከላከያ የሰሜን እዛ ላይ የተቀነባበረ ጥቃት በማደረስ ሀገር በመካዱ የፌደራል መንግስት የሀገሪቱን ህገመንግስታዊ ደህንነት ለመከላከል ሲል ወደ እርምጃ እንዲገባ አድርጎታል ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ለልኡክ ቡድኑ ህግ በማስከበር ዘመቻው ሰላማዊ ዜጎች እንዳይጎዱ ጥንቃቄ እንደሚደረግ፣ የሰብአዊ መብት እርዳታ የሚደረግባቸው መስመሮች በሰላም ሚኒስትር መለየታቸውን፤ የተፈናቀሉ ዜጎችን ለመቀባልና መድብለ ፓርቲ ያለው ጊዜያዊ የትግራይ አስተዳደር ለመመስረት እንደሚሰሩ ማስረዳታቸውን መግለጫው ጠቅሷል፡፡
ከዚህ በተጫማሪም በትግራይ የተጎዱ መሰረተ ልማቶችን እንደገና እንደሚገነቡም ለልኡክ ቡድኑ አባላት አስረድተዋል ብሏል መግለጫው፡፡
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል ያለው አለምግባባት ወደ ግጭት ያመራው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥቅምት 24 ህወሓት በክልሉ በሚገኙት የመከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ ጥቃት መሰንዘሩንና በህወሓት ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ከሳወቁ በኋላ ነው፡፡
በትናንትናው እለት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መከላከያ ሰራዊት በትግራይ ክልል እያካሄደ ያለውን “የህግ ማስከበር ዘመቻ” የመጨረሻ ምእራፍ እንዲያካሄድ መታዘዙን አስታውቀዋል፡፡
ግጭቱ ከተጀመረ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትግራይ በኩል ሆነው የትግራይ ልዩ ሃይል አባላትና ሚኒሻዎች በሰላም ለመከላከያ ሰራዊት እጅ እንዲሰጡ ሁለት የ72 ሰአታት የጊዜ ገደብ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ መከላከያ ሰራዊት ሰላማዊ ዜጎች በማይጎዱበት መልኩ ወንጀለኞችን ለመያዝ የሚያስችለውን ስልት ነድፏል፤ የመቀሌ ህዝብም ትጥቁን ፈቶ በቤቱ መቀመጥና ከወታደራዊ ኢላማዎች እንዲርቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፌደራል መንግስትና በትግራይ ክልል መካከል ያለው ግጭት ሶስት ሳምንት በላይ ሆኖታል፡፡