አዲስ አዛዥ ወደ ሰሜን ዕዝ የተላከው ጄነራል ድሪባ ከህወሓት ሰዎች ጋር ከተመገቡ በኋላ ስለታመሙ ነው
ጄነራል ጀማል የሰሜን እዝ አዛዥ ሆነው ሲላኩ ህወሓት አልቀበልም በማለታቸው ተመልሰው ነበር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ “ የራሳችን ካሃዲዎች ወታደሮቹን ራቁታቸውን ሲያባብሯቸው ኤርትራውያኖች“ ትብብር አድርገውላቸዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ “ የራሳችን ካሃዲዎች ወታደሮቹን ራቁታቸውን ሲያባብሯቸው ኤርትራውያኖች“ ትብብር አድርገውላቸዋል
ለሰሜን ዕዝ አዲስ አዛዥ ተልኮ የነበረው በመከላከያ ሰራዊት የሰሜን ዕዝ አባላት ጥቃቱ ከመፈጸሙ በፊት የሰሜን ዕዝ አዛዥ ጄኔራል የነበሩት ጀነራል ድሪባ መኮንን ከህወሃት ሰዎች ጋር ምሳ ከበሉ በኋላ ራሳቸውን በመሳታቸው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ገልጸዋል፡፡
ጀነራል ጀማል መሐመድ ወደ ሰሜን ዕዝ በተላኩበት ጊዜ የህወሃት ሰዎች አንቀበልም በሚል መመለሳቸው የሚታወስ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሰሜን ዕዝ አባላት ላይ የተደረገውን ግዲያ እና ከዛ በፊት የነበሩትን ሁኔታዎች ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አብራርተዋል፡፡
በሰሜን ዕዥ አባላት ላይ ተደርጎ ከነበረው ጥቃት በኋላ መንግስት የጀመረው የሕግ ማስከበር ሥራ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጉዳይ ሳይደርስ በሶስት ሳምንት ውስጥ ቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸው ይህ የሆነው ደግሞ መከላከያ ሰራዊቱ በጣም ዲሲፕሊን ያለው ጀግና ወታደር ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በርካታ ሮኬቶች እንዳሉት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሁንና ወደ ትግራይ አንድም ሮኬት አለመተኮሱን አንስተዋል፡፡ ይህም ተልዕኮው በኃላፊነት ስሜት መከናወኑን ያመለክታል ብለዋ፡፡
መቀሌ ከተማን ለመያዝ በተደረገው ተልዕኮ መካናይዝድ ኦፕሬሽን አለመሰራቱን አንስተው ይህ ያልተደረገው ከገንዘብ ጋር በተያያዘ ነው ብለዋል፡፡ የህወሃት ቡድን የሀገሪቱ አቅም ሰሜን ዕዝ ላይ እንዲሆን ሆን ብሎ አስቀድሞ ብዙ ስራ መስራቱንም በፓርላማ ገለጻቸው ወቅት አንስተዋል፡፡
ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም የህወሃት ቡድን በኢትዮጵያ ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ አጉል ስራ መስራቱን ጠቅሰው የሰሜን ዕዝ መብራት በጣጥሶ፣ ወታደሩ እንዳይገናኝ ግንኑነት መስመር በማቋረጥ፣ብዜዎችን በመግደል እንዲሁም በማፈን የተደረገው ስራ አስነዋሪ ነበር ብለዋል፡፡
የግንኙነት መስመር የቋረጠበትን ወደ ጎረቤት ሀገራት የሄዱትን እና ሌሎችንም በማሰባሰብ ተልዕኮውን በብቃት ማጠናቀቅ ተችሏልም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
የሰሜን ዕዝ አባላት ራቁታቸውን ወደ ኤርትራ በሄዱ ጊዜ በኤርትራውያን የሚለበስ ልብስ ማግኘታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
“የራሳችን ካሃዲዎች ወታደሮቹን ራቁታቸውን ሲያባብሯቸው ኤርትራዎቹ ግን አስፈላጊውን ትብብር አድርገውላቸዋል“ብለዋል፡፡ ከኤርትራ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ያደረገችውን ሕግ የማስከበር ስራ የደገፉት ጅቡቲ፣ ሱዳን፣ደቡብ ሱዳን፣ ኬንያ፣ ሶማሊያም ምስጋና ቀርቦላቸዋል፡፡
ከተጀመረ ወር ሊሆነው በተቃረበው የፌደራል መንግስትና የህወሓት ግጭት የፌደራል መንግስት የትግራይ ክልል ዋና ከተማ የሆነችውን መቀሌን በመጨረሻ ዘመቻ መቆጣጠሩን አስታውቋል፡፡