ሩሲያ፤ ከኔቶ ጋር በተያያዘ ያሳስበኛል ባለችው የደህንነት ስጋት ላይ ዋስትና እንድትሰጣት አሜሪካን ጠየቀች
የሃገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ስምምነት ላይ ያልደረሱበትን ውይይት በጄኔቭ አድርገዋል
ዋሽንግተን በበኩሏ ሞስኮው ዩክሬንን የምትወር ከሆነ ፈጣንና ከባድ አጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቃለች
ሩሲያ፤ ከዩክሬን እና ኔቶ ጋር በተያያዘ ያሳስበኛል ላለችው የደህንነት ስጋት ዋስትና እንድትሰጣት አሜሪካን ጠየቀች፡፡
ሞስኮው አለብኝ ካለችው ስጋት ጋር በተያያዘ ዋሽንግተን እስከ ቀጣዩ ሳምንት ድረስ በጽሁፍ የተረጋገጠ ዋስትናንት እንድትሰጣት ጠይቃለች፡፡
የሃገራቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ሰርጌይ ላቭሮቭ እና አንቶኒዮ ብሊንከን ዛሬ አርብ በስዊዘርላንድ ጄኔቭ ተገናኝተው መክረዋል፡፡
ሆኖም ዩክሬንን እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር (ኔቶ)ን ተቀዳሚ አጀንዳ ባደረገው ምክክር ላለመስማማት ተስማምተው ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮቹ የተገናኙት፡፡ ውጥረቱን ለማርገብ በማሰብ ከመገናኘት ውጭ የደረሱበት ስምምነትም የለም፡፡ ነገር ግን ሰርጌይ ላቭሮቭ ውይይቱ “ገንቢ እና ጠቃሚ ነበር” ብለዋል፡፡
ሃገራቸው ከዩክሬን እና ኔቶ ጋር በተያያዘ አለኝ ባለችው ስጋት ላይ አሜሪካ እስከ ቀጣዩ ሳምንት ድረስ የማረጋገጫ ዋስትናን በጽሁፍ ለመስጠት መስማማቷንም ተናግረዋል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፡፡
የመነጋገራቸው ውጤት ከዚያ በኋላ የሚታይ መሆኑንም ነው ላቭሮቭ የገለጹት፡፡
ዩክሬንን የመውረር እቅድ እንደሌላት በውይይቱ የገለጸችው ሩሲያ ለደህንነቷ የኔቶ ጉዳይ ያሳስባታል፡፡ ሞስኮው ዩክሬን የኔቶ አባል እንደማትሆንና ቃል ኪዳን ጦሩ በምስራቃዊ አውሮፓ በተለይም የቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት አካል ወደነበሩ ሃገራት መስፋፋቱን እንደሚያቆም የሚያረጋግጥ ዋስትና ትፈልጋለች፡፡
ሞስኮው ኔቶ ቡልጋሪያ እና ሮማኒያን ጨምሮ ከፈረንጆቹ 1997 በፊት አባላቱ ካልነበሩት ሃገራት ከነ ጦር መሳሪያዎቹ ለቆ እንዲወጣም ነው አጥብቃ የምትፈልገው፡፡ ሆኖም ዋሽንግተንና የአውሮፓ አጋሮቿ ይህን አይቀበሉም፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ከላቭሮቭ ጋር ተገናኝተው ከመወያየታቸው በፊት በዩክሬን፣በፈረንሳይ፣ በእንግሊዝ እና በጀርመን ጉብኝት አድርገዋል፡፡
አሜሪካ ለዲፕሎማሲያዊ መፍትሔዎች ዝግጁ መሆኗን የተናገሩት ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሩሲያ ዩክሬንን የምትወር ከሆነ ሃገራቸው ፈጣንና ከባድ ፈጣንና ከባድ አጸፋዊ እርምጃ እንደምትወስድ አሳስበዋል፡፡
ሀገራቱ ልዩነታቸውን በውይይት ለመፍታት ባይችሉ እንኳ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች እንዲቀጥሉ መናገራቸውንም ነው ሲ.ኤን.ኤን የዘገበው፡፡
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ትናንት ሃሙስ ፑቲን ዩክሬንን የሚወር ከሆነ “ከባድ ዋጋ ይከፍላል” ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል፡፡