“ኔቶን ስለመቀላቀል ስላለመቀላቀላችን ሩሲያ አትወስንልንም”- የዩክሬን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ከሰሞኑ በጄኔቫ በምስራቃዊ ዩክሬን ጉዳይ ከሩሲያ ጋር መወያየታቸው ይታወሳል
ሚኒስትሩ የሩሲያ “የህጋዊ ዋስትና ጥያቄ በምዕራቡ ዓለም ተቀባይነት የሌለው ነው” ብለዋል
ሩሲያ የዩክሬን ኔቶን መቀላቀል በተመለከተ የመወሰን “ምንም አይነት መብት የላትም” ሲሉ የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ተናገሩ፡፡
ኤ.ኤፍ.ፒ የዩክሬኑን አር.ቢ.ኬ የዜና ጣቢያ ዋቢ በማድረግ እንደዘገበው፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኩሌባ በሰጡት ጠጠር ያለ አስተያየት “ሩሲያ በዩክሬን የኔቶ አባልነት ጉዳይ ላይ የመምረጥ መብት የላትም፤ ይህ እኛም ሆንን አጋሮቻችን የማያስነኩት 'ቀይ መስመር' ነው” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
ሚኒስትሩ አክለውም “የተባበረው የምዕራቡ ዓለም ኅብረት ሩስያ በስተምስራቅ በኩል ላላት የመስፋፋት ፍላጎት ‘ህጋዊ ዋስትናዎች’ አይስማማም ፣ ምክንያቱም ይህ ዋናው የሩሲያ ስትራቴጂካዊ ሽንፈት መሆኑ ይታወቃል” ብለዋል።
ሚኒስትሩ እንዲህ ቢሉም፤ ሞስኮ ግን ከዋሽንግተን እና የኔቶ አጋሮቿ ሰፊ የደህንነት ዋስትና ጠይቃ ፤ህብረቱ ወደ ምስራቅ እንደማይስፋፋ ቃል እንደተገባላት ስትናገር ትደመጣለች።
የኩሌባ አስተያየት፤ ሰሞኑን በምስራቅ ዩክሬን ጉዳይ በምዕራቡ ዓለምና ሩሲያ መካከል ያለውን ውጥረት እየተባባሰ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ጉዳዩን የበለጠ ያባብሰዋል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡
አሜሪካ እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት /NATO/ ዩክሬንን እና ጆርጅያን እንደ አዲስ በአባልነት ከተቀበሉ የሀገራቱ አባልነትን ምክንያት በማድረግ በቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ምድር የጦር ሰፈር የመገንባት እቅድ እንዳላቸው ይነገራል፡፡
ይሁን እንጅ ይህ የአሜሪካ እና የኔቶ እቅድ ፈጽሞ ተቀባይነት እንደሌለው ሩሲያ ስትገልጽ ቆይታለች፡፡
በዚህ ሳምንት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ልትፈጽም ትችላለች በሚል ፍራቻ ፤ምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ከሰሞኑ ከሩሲያ አቻዎቻቸው ጋር በጄኔቭ መመክራቸው ይታወሳል፡፡
ለሰባት ሰአታት ከዘለቀው የጀኔቭ ድርድር አዲስ ነገር ቢጠበቅም፤ ድርድሩ እንደሚቀጥል ከመግለጽ ውጭ የተሰጠ ዝርዝር ማብራሪያ የለም፡፡ የኔቶ እና ሩሲያ ምክር ቤት ስብሰባ ነገ ረቡዕ እንደሚካሄድም ይጠበቃል፡፡
በፈረንጆቹ 2014 ሩሲያ የክሬይሚያን ልሳነ ምድር ከዩክሬን ተቆጣጥራ የቆየች ሲሆን ፤በምስራቃዊ ዩክሬን የሚንቀሳቀሰውን አማፂ ቡድን ትደግፋለች የሚል ክስ ሲቀርብባት ይስተዋላል፡፡
በምስራቅ ዩክሬን ያለው ግጭት እስካሁን ከ13 ሺህ በላይ ሰዎችን ህይወት ቀጥፏል።