ሰርጌ ላቭሮቭ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት አምባሰደሮች ጋር ይመክራሉ
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለይፋዊ የስራ ጉብኝት አዲስ አበባ ሊመጡ መሆኑ ተገለፀ።
በአዲስ አበባ የሩሲያ ኤምባሲ ለአል ዐይን አማርኛ እንዳስታወቀው ሰርጌ ላቭሮቭ የፊታችን ማክሰኞ ሐምሌ 19 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ ይገባሉ።
የውጭ ጉጋይ ሚኒስትሩ የሁለት ቀናት ቆይታ እንደሚኖራቸውም አስታውቋል።
የኤምባሲው ፕሬስ አታቼ ማሪያ ቸርኑኪና ለአል ዐይን እንዳሉት ዲፕሎማቱ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከአፍሪካ ህብረት ተወካዮች፣ ከኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት እና ከተለያዩ ሀገራት የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ጋር ይወያያሉ ተብሏል።
ላቭሮቭ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚሰጡም ፕሬስ አታቼ ማሪያ ቸርኑኪና አስታውቀዋል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከኢትዮጵያ በተጨማሪም በግብፅ፣ በኡጋንዳ እና በኮንጎ ሪፐብሊክ ጉብኝት እንደሚያደርጉም በአዲስ አበባ የሩሲያ ኤምባሲ አክሎ አስታውቋል
ኢትዮጵያ እና ሩሲያ ረጅም ዘመን ያስቆጠረ ወዳጅነት ያላቸው ሲሆን፤ በቅርቡም የሩሲያ ዩክረን ጦርነትን ተከትሎ በርካታ ኢትዮጵያውያን ለሩሲያ ያላቸውን አጋርነት ማሳየታቸውን ኤምባሲው መግለጹ ይታወሳል።
የኤምባሲው ፕረስ አታቼ ማሪያ ቸርኑኪና በወቅቱ ለአል ዐይን እንዳስታወቁት፤ “በርካታ ኢትዮጵያዊያን በኢሜይል እና በአካል ከሩሲያ ጎን መሆናቸውን እያሳወቁን ነው ለዚህ እናመሰግናለን” ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ይሄንን እያደረጉ ያለው ረጅም እና ታሪካዊ በሆነው የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ወዳጅነት ላይ ስለሚተማመኑ እንደሆነም ኤምባሲው መግለፁ አይዘነጋም።