ሩሲያ ኢትዮጵያውያን ወዶ ዘማቾችን እየመለመለች ነው መባሉን አስተባበለች
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ መግቢያ በር ላይ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተሰልፈው ታይተዋል
የሩሲያ ኤምባሲ በር ላይ ኢትዮጵያዊያኑ ለምን ተሰለፉ ለሚለው ኤምባሲው አል-ዐይን አማርኛ ማብራሪያ ሰጥቷል
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ መግቢያ በር ላይ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ሩሲያን ወግነው ዩክሬንን ለመውጋት ለመመዝገብ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ ናቸው የሚል ምስል በማህበራዊ የትስስር ገጾች ላይ በመሰራጨት ላይ ይገኛል፡፡
አል ዐይን አማርኛ ጉዳዩን በሚመለከት በአዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ ጠይቋል።
የኤምባሲው ፕረስ አታቼ ማሪያ ቸርኑኪና ለአል ዐይን እንዳሉት “ሩሲያ ለዩክሬን ጦርነት ኢትዮጵያዊያንን ለመቅጠር ማስታወቂያ አላወጣችም፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለው መረጃም ሀሰተኛ ነው” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል።
ነገርግን ኢትዮጵያውን ወደ ኢምባሲው መሄዳቸው እውነት መሆኑን ኢምባሲው ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያውያን ወደ ሩሲያ ኢምባሲ የሄዱት ለምልመላ ሳይሆን ለሩሲያ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት መሆኑን የኤምባሲው ፕረስ አታቼ ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት “በርካታ ኢትዮጵያዊያን በኢሜይል እና በአካል ከሩሲያ ጎን መሆናቸውን እያሳወቁን ነው ለዚህ እናመሰግናለን” ሲሉም አክለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ይሄንን እያደረጉ ያለው ረጅም እና ታሪካዊ በሆነው የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ወዳጅነት ላይ ስለሚተማመኑ እንደሆነም ኤምባሲው ተገልጿል።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ሩሲያ እና ዩክሬን ይፋዊ ጦርነት ከጀመሩ 54ኛ ቀኑን ይዟል።
እስካሁን ባለው ሂደት አምስት ሚሊየን ገደማ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ሲሰደዱ በርካቶች ደግሞ ህይወታቸውን አጥተዋል።
ሩሲያ ከ23 ሺህ በላይ የዩክሬን ወታደሮችን እንደገደለች የተናገረች ሲሆን ዩክሬን በበኩሏ 20 ሺህ የሩሲያ ወታደሮችን ገድያለሁ ማለቷ ይታወሳል።