በአዲስ አበባ የሚገኙት የሩሲያ እና የዩክሬን ኤምባሲዎች ተቃራኒ ሃሳብ እየሰጡ ነው
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በማካሄድ ላይ ባለችው ጦርነት ኢትዮጵያውያንን ከጎኗ ለማሰለፍ ጥረት እያደረገች መሆኗ በኢትዮጵያ የዩክሬን ኤምባሲ አስታወቀ፡፡
ኤምባሲው ሩሲያ ኢትዮጵያውያን ወጣቶችን እየመለመለች ነው ሲል ስለ ጉዳዩ ለጠየቀው አል ዐይን አማርኛ አስታውቋል፡፡
ከሰሞኑ በአዲስ አበባ በሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ መግቢያ በር ላይ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ተሰልፈው መታየታቸው ሲያነጋግር ነበረ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ "ከሩሲያ ጋር ጎን ተሰልፈው በጦርነቱ ለመሳተፍ ለመመዝገብ የተሰለፉና ወረፋ የሚጠብቁ ናቸው" የሚሉ መረጃዎች በተለያዩ የማህበረሰብ ትስስር ገጾች ሲዘዋወሩም ነበረ፡፡
ሆኖም ከአል ዐይን አማርኛ ጋር የስልክ ቆይታ ያደረጉት የሩሲያ ኤምባሲ ፕሬስ አታሼ ማሪያ ቸርኑኪና “ሩሲያ ለዩክሬን ጦርነት ኢትዮጵያዊያንን ለመቅጠር ማስታወቂያ አላወጣችም፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች እየተሰራጨ ያለው መረጃም ሀሰተኛ ነው” ሲሉ ትናንት ሰኞ መረጃውን ማስተባበላቸው ይታወሳል፡፡
በኢትዮጵያ የዩክሬን ኤምባሲ ግን በማስተባበያው አያምንም፡፡ ”በተለያዩ የማህበረሰብ ትስስር ገጾች እየተሰራጨ ያለው መረጃ ሀሰተኛ ነው” መባሉ ”በራሱ ውሸት ነው” ሲልም ነው ኤምባሲው ለአል ዐይን የገለጸው፡፡
ሩሲያ አሁን ላይ ከኢትዮጵያ ወጣቶችን ለመመልመል ሙከራ እያደረገች ትገኛለችም ብሏል ኤምባሲው፡፡
የኤምባሲው የሚሽን ሃላፊ አሌክሳንደር ከሰሞኑ አንድ የሩሲያን ወታደራዊ የደንብ ልብስ (ዩኒፎርም) የለበሰ ሰው አዲስ አበባ ገብቷል ሲሉ ነው ለአል ዐይን የተናገሩት፡፡
የሰውዬው መግባት ከጉዳዩ ጋር ምን እንደሚያገናኘው ለቀረበላቸው ጥያቄ”ዩኒፎርም የለበሰው ወታደር መቼም በግ ጠባቂ አይደለም፣ ወታደር እንጅ” ሲሉ መልሰዋል ፡፡
ሩሲያ ”70 በመቶ የሚሆነው ጦሯ አልዋጋም ስላላት ኢትዮጵያውንን ለመመልመል ጥረት እያደረገች ቢሆንም ኢትዮጵያውያን ግን ፈቃደኛ አልሆኑላትም” ሲሉም ነው አሌክሳንደር የተናገሩት፡፡
ኢትዮጵያውያን አዲስ አበባ ወደሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ የሄዱት ለምልመላ ሳይሆን ለሩሲያ ያላቸውን አጋርነት ለማሳየት መሆኑን የኤምባሲው ፕሬስ አታሼ ቢገልጹም፤ በአዲስ አበባ የዩክሬን ኤምባሲ ግን ሞስኮ ምልመላ ለማድረግ እየሞከረች ነው ብሏል፡፡
ሩሲያ ”የተለያዩ መደለያዎችን እሰጣለሁ” በማለት ኢትዮጵያውያንን ለመመልመል ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ መስማታቸውንም ነው የሚሽን ኃላፊው የገለጹት፡፡
ሩሲያ ከዩክሬን ጋር እያደረገችው ባለው ጦርነት “በርካታ ኢትዮጵያውያን በኢ-ሜይል እና በአካል ከሩሲያ ጎን መሆናቸውን እያሳወቁን ነው ለዚህ እናመሰግናለን” ሲሉም አክለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ይሄንን እያደረጉ ያለው ረጅም እና ታሪካዊ በሆነው የኢትዮጵያ እና ሩሲያ ወዳጅነት ላይ ስለሚተማመኑ እንደሆነም ኤምባሲው ገልጿል።
ኤምባሲው በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድን እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ይፋዊ ገጾች በመጥቀስ ‘እወቁት’ በሚመስል መልኩ ስለ ሁኔታው ጽፏል፡፡
በአዲስ አበባ የሚገኙት የሩሲያ እና የዩክሬን ኤምባሲዎች የሰጧቸውን አስተያየቶች ተከትሎ አል ዐይን አማርኛ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎችን ለማነጋገር ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ጦርን ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ሩሲያ እና ዩክሬን ይፋዊ ጦርነት ከጀመሩ 55 ኛ ቀኑን ይዟል።