ደብዳቤው ተጨማሪ ድጋፍ ላጸደቀው የአሜሪካ መንግስት የተጻፈ ነው
ሩሲያ፣ ሩሲያን ማስታጠቋን እንድታቆም የሚያስጠነቅቅ ደብዳቤ ለአሜሪካ ጻፈች፡፡
ይፋዊ ነው የተባለለት ደብዳቤው ዩክሬንን ለማስታጠቅ ከአሜሪካ እና ከኔቶ የሚጫነው ጦር መሳሪያ ውጥረቱን ከማባባስ ባለፈ ወዳልተጠበቀ አቅጣጫ የሚያመሩ ሁኔታዎችን ሊፈጥር እንደሚችል ያሳስባል፡፡
ዋሽንግተን ፖስት አየሁት ባለው ደብዳቤ ላይ ሩሲያ የጦር መሳሪያዎች ዝውውርን በተመለከተ የተቀመጡ ዓለም አቀፍ ህግጋትን የሚጥስ ነው በሚል የአሜሪካንና የአጋሮቿን እርምጃ ኮንናለች፡፡
ሩሲያ ከ23 ሺህ በላይ የዩክሬን ወታደሮችን ገድያለሁ አለች
የተጀመረ የሰላም ጥረቶች እያስተጓጎለ ነው ስትልም ነው ሞስኮ የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶን የከሰሰችው፡፡
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) ባሳለፍነው ማክሰኞ የተጻፈ ነው ስለተባለለት ደብዳቤ ምንም ያለው ነገር የለም፡፡
ሆኖም አሜሪካና የኔቶ አጋሮቿ ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን ተከትሎ በቢሊዮን ዶላሮች የሚቆጠር ዋጋ ያለው ወታደራዊ ድጋፍ እያደረጉ መሆኑን የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ገልጸዋል፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ አሜሪካና አጋሮቿ ዘርፈ ብዙ ማዕቀቦችንና የሃብት እገዳዎችን በሩሲያ ላይ ጥለዋል፡፡ ሩሲያም በበኩሏ በ398 የአሜሪካ ምክር ቤት አባላት ላይ ማዕቀብ መጣልን ጨምሮ የተለያዩ የአጸፋ እርምጃዎችን ወስዳለች፡፡
ቅጥረኞችን ጨምሮ ከ23 ሺህ በላይ የዩክሬን ወታደሮችን ገድያለሁ ስትል ማስታወቋም የሚታወስ ነው፡፡
ለነጩ ቤተ መንግስት ተጻፈ የተባለው ደብዳቤ የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር ለዩክሬን ተጨማሪ የ800 ሚሊዮን ዶላር ድጋፍ ማጽደቁን ተከትሎ ነው እንደ ዋሽንግተን ፖስት ዘገባ፡፡
ድጋፉ 11 የጦር ሂሊኮፕተሮችን፣ 300 ሰው አልባ አውሮፕላኖችን (ድሮን)፣ 200 ብረት ለበስ ተሽከርካሪዎችን፣ 18 ሃውትዘር እና 40,000 የመድፍ ጥይቶችን፣ 10 ፀረ-መድፍ ራዳሮችን፣ 500 ጃቭሊን ሚሳኤሎችን፣ ሰው አልባ የባህር ዳርቻ ቅኝት መርከቦችን እና ምናልባት የሚያጋጥም ከሆነ ከኬሚካል ጦር መሳሪያዎች ጥቃት ራስን ለመጠበቅ የሚያስችሉ ወታደራዊ ቁሳቁሶን ያካትታል፡፡