የኋይት ሀውስ ጠበቆች ፕሬዚዳንቱን መከላከል ጀምረዋል፡፡
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከስልጣን እንዲነሱ በኮንግረሱ ድምጽ ከተሰጠ በኋላ በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ዉሳኔ ለመስጠት ሴኔቱ በመመልከት ላይ ሲሆን የትራምፕ ጠበቆች ትራምፕ የቀረበባቸው ክስ ሀሰት መሆኑን ለሴኔቱ በማስረዳት ላይ ናቸው፡፡
ትናንት ጥር 16 ቀን 2012 ዓ.ም “የትራምፕ እጣ ፋንታ መወሰን ያለበት በህዝብ ድምጽ ነው” ያሉት ጠበቆቹ፣ “ሴኔቱ ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን እንዲነሳ የሚወስን ከሆነ ድርጊቱ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ይሆናል” ብለዋል፡፡
በነጩ ቤተ መንግስት የህግ አማካሪ ሆኖ በማገልገል ላይ የሚገኘው ፓት ሲፖሎን በ100 ሴናተሮች ፊት ቀርቦ ባደረገው ንግግር “ዲሞክራቶች በአሜሪካ ታሪክ ተደርጎ የማይታወቅ ውሳኔ እንድታስተላልፉ ነው የሚጠይቋችሁ፤ ለሚያቀርቡት ክስ እንኳን በቂ ማስረጃ የላቸውም” ሲል ተናግሯል፡፡
“እውነቱን ስትሰሙ ፕሬዝዳንቱ ምንም ወንጀል እንዳልሰሩ ታረጋግጣላችሁ” ሲልም ሲፖሎን ተናግሯል፡፡
የጠበቆቻቸው ቃል መሰማት ከመጀመሩ በፊት ክሱን የሚያስተባብሩ የዲሞክራት ፓርቲ አመራሮችን በመዝለፍ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ተደጋጋሚ ጽሁፎችን በትዊተር ገጻቸው አስነብበዋል፡፡
ጠበቆቹ ትናንት ፕሬዝዳንቱን መከላከል ከመጀመራቸው በፊት በነበሩት ሶስት ቀናት፣ የዲሞክራቶች ተወካዮች የፕሬዝዳንቱን ሁለት ክሶች ለሴኔቱ አቅርበዋል፡፡
የዲሞክራቶች ተወካዮች የክስ ዶክመንት ይዘው ወደ ሴኔት ሲገቡ
ከሁለቱ ክሶች አንዱ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለዩክሬይን ወታደራዊ ድጋፍ እንደ እጅ መንሻ በመስጠት፣ በሀገሪቱ በሚገኘው የነዳጅ ኩባኒያ ከሚሰራው የ ጆ ባይደን ልጅ ጋር በማያያዝ፣ የቀድሞ ተቀናቃኛቸው የዲሞክራቱ ጆ ባይደን በምርጫው ጣልቃ እንደገቡ የሚያሳይ ሴራ ዩክሬይን እንድታዘጋጅና ክስ እንድትመሰርት ጠይቀዋል የሚል ነው፡፡ ይሄም ፕሬዝዳንቱ ከምርጫ 2016 ጋር በተያያዘ ከሩሲያ ጋር ነበራቸው የሚለውን ውንጀላ ለመቀልበስ አስበው ያሴሩት ነው ሲሉ ዲሞክራቶች ከሰዋል፡፡
ሁለተኛው ክስ ደግሞ በኮንግረሱ ያሉ ደጋፊዎቻቸውን በመጠቀም ኮንግረሱ ክሳቸውን እንዳይቀበል ለማድረግ በኮንግረሱ ስራ ጣልቃ ገብተዋል የሚል ነው፡፡
የትራምፕ ጠበቆች ነገ ሰኞ እለት ጥር 18 ቀን 2012 ዓ.ም ፕሬዝዳንቱን ለመከላከል የሚያደርጉትን ንግግር ይቀጥላሉ የተባለ ሲሆን ለዚህም 24 ሰዓት ይሰጣቸዋል፡፡
ከዚህ ሂደት በመቀጠል ለ16 ሰዓታት ሴኔቱ ሁለቱንም አካላት ያካተተ የጥያቄና መልስ ቆይታ ያደርጋል፡፡
አስፈላጊ የምርመራ ሂደቶችን ጨርሶ፣ ሴኔቱ በፕሬዝዳንቱ ቀጣይ እጣ ፋንታ ላይ በተያዘው ወር የመጨረሻ ቀናት የመጨራሻ ውሳኔ ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ምንጭ፡- ሲጂቲኤን