ቭላድሚር ፑቲን፤ የአፍሪካ ቀንን በማስመልከት መልዕክት ላኩ
የኢትዮጵያ እና ግብፅ መሪዎችም በአፍሪካ ሀገራት መካከል አንድነትና ህብረት እንዲጠናከር ይሰራል ብለዋል
ፑቲን በመልዕክታቸው ሀገራቸው ከአፍሪካ ጋር በጋራ እንደምትሰራ አስታውቀዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን፤ የአፍሪካ ቀንን በማስመልከት ለአፍሪካ ህብረት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ላኩ፡፡
ቀኑን በማስመልከት በአህጉሪቱም ከአሁጉሪቱም ውጭ ለሚገኙ አፍሪካውያን እንኳን አደረሳችሁ ያሉት የአፍሪካ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበር የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ብሩህ ራዕን አንግበው ፓን አፍሪካኒዝምን በማቀንቀን የአፍሪካ አንድነት (ህብረት) ድርጅትን ለመመስረት ያስቻለውን ችቦ ከ59 ዓመታት በፊት የለኮሱትን መስራች አባቶች አመስግነዋል፡፡
የህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ቀኑን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት ሙስና፣ የእርስ በእርስ ግጭቶች፣ ሕገ ወጥ የመንግስት ለውጥ የአህጉሩ ፈተናዎች መሆናቸው ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም የአፍሪካን ቀን በማስመልክት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን በይፋዊ የማህበረሰብ ትስስር ገጾቻቸው አስተላልፈዋል፡፡
የቀደሙ የፓን አፍሪካ አባቶች ራዕይ አንድነት መሆኑን ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ራዕዩን እውን ለማድረግ እንደሚሰራ "እናረጋግጣለን" ብለዋል በመልዕክታቸው ፡፡
ቭላድሙር ፑቲን ደግሞ በመልዕክታቸው ሀገራቸው ከእስከዛሬው በበለጠ ከአፍሪካ ጋር በጋራ በትብብር ለመስራት ዝግጁ መሆኗን አስታውቀዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ የአፍሪካ ቀንን በማስመልከት በላኩት መልዕክት፤ አፍሪካ በዓለም መድረክ ጠቃሚ ጉዳዮችን እያነሳች መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስሙን ወደ አፍሪካ ሕብረት ከቀየረ 20ኛ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በነዚህ ሁለቱ አስርት ዓመታት አፍሪካ በጋራ ትልቅ ስራ መስራቷንም ነው የሩሲያው ፕሬዝዳንት የገለጹት፡፡
በአህጉሩ ለተከሰቱ ግጭቶችና የቀውስ ሁኔታዎች የአፍሪካ ሀገራት መንግስታት ምላሽ ለመስጠት መሞከራቸውን ያነሱት ፑቲን፤ ባለፉት ዓመታት ቀጠናዊ ትብብርን ለማስተዋወቅ መሰራቱን በመልዕክታቸው አንስተዋል፡፡
አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተጽዕኖ እያደገ መምጣቱን የገለጹት ፑቲን፤ ጠቃሚ ዓለም አቀፍ አጀንዳዎችንም እያነሳች ትገኛለች ብለዋል፡፡ ሩሲያ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ያላትን ወዳጅነትና ትብብር እንደምታጠናክርም ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት፡፡ በቀጣይ በጋራ ፕሮጄክቶች ላይ እንሰራለንም ብለዋል፡፡
በ2019 የተካሄደው የሩሲያ አፍሪካ ጉባዔ ሁለቱ ወገኖች በሁለትዮሽና በባለብዙ ወገን ፍሬያማ ትብብር እንዲኖራቸው ዕድል መፍጠሩንም ቭላድሚር ፑቲን የገለጹት፡፡
የግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ በበኩላቸው ቀኑ በአህጉሪቱ ሀገራት መካከል አንድነት እና ትብብር እንዲኖር የሚያደርግ መሆኑን ጠቅሰው፤ ግብፅ ዘላቂ ልማትና ትብብርን ለማምጣት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት በጋራ ትሰራለች ብለዋል፡፡