የዩክሬን ፕሬዝዳንት በአፍሪካ ህብረት ንግግር ለማድረግ ጠየቁ
አፍሪካ ከዩክሬን- ሩሲያ ጦርነት ጋር በተያያዘ ያላትን አቋም እንድታሳውቅ ውትወታዎች በርትተዋል
ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ህብረቱን ለማነጋገር መጠየቃቸውን የህብረቱ ሊቀመንበር ማኪ ሳል አስታውቀዋል
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዘለንስኪ በአፍሪካ ህብረት ንግግር ለማድረግ ጠየቁ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ለህብረቱ ሊቀመንበር ለሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ደወለው በዚህና በሌሎች ሃገራቸው ከሩሲያ ጋር ከገባችበት ጦርነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ማውራታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ህብረቱ ዓለም አቀፍ ህግጋት እንዲከበሩ በማሳሰብ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሄዎች ይፈለጉለት ሲል መግለጫ ማውጣቱን ያደነቁት ዘለንስኪ በመግለጫው ለዩክሬን ሉዓላዊነት እና ግዛታዊ አንድነት ስላሳየው ክብር ማመስገናቸውንም በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ አስታውቀዋል፡፡
አስበው በመደወላቸው ዘለንስኪን ያመሰገኑት ማኪ ሳል በበኩላቸው ጦርነቱ በራሷ በዩክሬን እና በዓለም ምጣኔ ሃብት ላይ ስላሳረፈው አሉታዊ ተጽዕኖ እንዲሁም ጦርነቱ በንግግር እልባት ሊያገኝ በሚችልበት መንገዶች ዙሪያ ማውራታቸውን ገልጸዋል፡፡
ቮሎዲሚር ዘለንስኪ ህብረቱን ለማነጋገር ያቀረቡትን ጥያቄ መመልከታቸውንም ነው ማኪ ሳል ያስታወቁት፡፡ ሆኖም ጥያቄው ተቀባይነት ስለማግኘቱ የታወቀ ነገር የለም፡፡
የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት የዓለምን የፖለቲካ አሰላለፍ እና የኃይል ሚዛን እየቀየረ ይሆን?
ሁኔታዎችን በአንክሮ እየተከታተለች መሆኑን በመግለጽ ሁሉም አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ የጠየቀችውን ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ ሃገራት ሩሲያ ከዩክሬን ጋር የገባችበት ጦርነት እንዲቆም ጠይቀዋል፡፡
ሆኖም ልክ እንደነ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሃገራት ሁሉ በይፋ ሩሲያን አውግዘው ተቃውሟቸውን ሲገልጹም ሆነ እርምጃዎችን ሲወስዱ አልታዩም፡፡ ይህም ምዕራባዊ ሃገራትን ደስ አላሰኘም፡፡ አፍሪካ አቋሟን በይፋ እንድታሳውቅና ጠንካራ ምላሾችን እንድትሰጥም በአሜሪካ ጭምር ውትወታዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
የጸጥታው ምክር ቤት ወረራውን በተመለከተ በድንገት በተሰበሰበበት መድረክ በይፋ ሩሲያን ካወገዘችው ከኬንያ ውጭ እስካሁን ደፍሮ የሞስኮን እርምጃ በግልጽ በአደባባይ ለማውገዝም ሆነ ከዩክሬን ጎን ነኝ ለማለት የደፈረ አፍሪካዊ ሃገርም የለም፡፡
የአፍሪካ ሀገራት ሩሲያን እንዲያወግዙ አሜሪካ ጠየቀች
ፓኪስታን፤ ሩሲያን እንድታወግዝ በ22 ሀገራት ዲፕሎማቶች ተጠየቀች
ቮሎዲሚር ዘለንስኪ የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በተለያዩ የውጭ ሃገራት ምክር ቤቶች ኪቭ ከሚገኘው ቤተመንግስታቸው ሆነው የበይነ መረብ ንግግርን አድርገዋል፡፡ በንግግራቸውም የብዙዎቹ ሃገራት የምክር ቤት አባላት ቆመው አጨብጭበውላቸዋል፡፡ንግግሩ ስለ ጦርነቱ በማውራት በማግባባትና በማሳመን ሃገራቱን ከዩክሬን ጎን ለማሰለፍ በማሰብ የሚደረግ ነው፡፡
እስካሁንም የአሜሪካ ህግ መወሰኛ ምክር ቤት (ሴኔት)ን ጨምሮ በአውሮፓ ህብረት፣ በእንግሊዝ፣በጀርመን፣ በካናዳ፣ በአውስትራሊያ፣ በእስራኤል እና በሌሎች ሃገራት ምክር ቤቶች ንግግር አድርገዋል፡፡
አሁንም በአፍሪካ ህብረት ንግግር የሚያደርጉበትን እድል የሚያገኙ ከሆነ የህብረቱን አባል ሃገራት በማግባባትና በማሳመን ከጎናቸው ለማሰለፍ የሚያስችል ንግግርን እንደሚያደርጉ ይጠበቃል፡፡