የሱዳን ተቃዋሚዎች በተመድ እና በአፍሪካ ህብረት የቀረበውን የ‘እናደራድራችሁ’ ጥያቄ ሳይቀበሉ ቀሩ
በጦሩ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳም ነው ተቃዋሚዎቹ የጠየቁት
ተቃዋሚዎቹ ከድርድሩ በፊት ጦሩ ስልጣን እንዲያስረክብ ጠይቀዋል
የሱዳን ተቃዋሚዎች በተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና በአፍሪካ ህብረት የቀረበላቸውን የየ‘እናደራድራችሁ’ ጥያቄ ሳይቀበሉ ቀሩ፡፡
ተቃዋሚዎቹ ከድርድሩ በፊት ሊተገበሩ ይገባል ያሏቸውን ቅድመ ሁኔታዎች አስቀምጠዋል፡፡
ከቅደመ ሁኔታዎቹ አንዱ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ይመራ የነበረውን የሲቪሊያን አስተዳደር ከሽግግር መንግስቱ አስወግዶ ስልጣን የያዘው የሃገሪቱ ጦር ስልጣኑን ያስረክብ የሚል ነው፡፡
በሌ/ጄ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው የሃገሪቱ ጦር ባሳለፍነው ወርሃ ጥቅምት መጨረሻ "የእርምት ነው" በሚል በወሰደው እርምጃ የሃምዶክን አስተዳደር በአዲስ መተካቱ ይታወሳል፡፡
“በምርጫ ካልሆነ በስተቀር ስልጣን አሳልፈን አንሰጥም”- የሱዳን ጦር መሪ
ይህን ተከትሎ ሱዳናውያን ወደ አደባባዮች በመውጣት ተቃውሟቸውን ሲገልጹም ነበረ፡፡ ተቃውሞውን ተከትሎም ሱዳን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ለመቆየት ተገዳለች፡፡
በተለያዩ ጊዜያት የተካሄዱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ በተቀሰቀሱ ግጭቶች 90 ሱዳናውያን ሲሞቱ 3 ሺ ገደማ መጎዳታቸውም ተነግሯል፡፡
በሃገሪቱ ሙሉ የሲቪሊያን መንግስት ነው ሊመሰረት የሚገባው ያሉት ተቃዋሚዎች የቡርሃን ወታደራዊ መንግስት የጣለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያነሳም ጠይቀዋል፡፡
ቡርሃን ወታደራዊ እርምጃውን ተከትሎ የታሰሩ ፖለቲከኞችን እንደሚፈቱ ከሰሞኑ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በልዩ መልዕክተኛው ቮከር ፐርዝስ በኩል የሱዳን ኃይሎች እንዲቀራረቡ ለማድረግ የተለያዩ ጥረቶችን እያደረገ እንደሚገኝ ከአሁን ቀደም አስታውቋል፡፡
ሆኖም ሱዳን ልዩ መልዕክተኛው ቮከር ፐርዝስ በራሴ ውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እየገቡ ነው ስትል ደጋግማ ከሳለች፡፡ ከሃገሯ ልታባርራቸው እንደምትችልም ነው ስታሳስብ የነበረችው፡፡
የሃገሪቱ ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት መሪ አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን በዚሁ ጉዳይ ላይ ልዩ መልዕክተኛውን አነጋግረው እንደነበር ይታወሳል፡፡