ኢራን በወቅታዊው የእስራኤልና ሄዝቦላህ ግጭት ምን አለች?
የኢራኑ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ “የሄዝቦላህን መሪዎች መግደል ቡድኑ እንዲንበረከክ አያደርገውም” ብለዋል
ቴህራን ሄዝቦላህ ከተመሰረተበት 1982 ጀምሮ ወታደራዊና የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግለት ይነገራል
የሄዝቦላህ መሪዎችን መግደል ቡድኑ እንዲሸነፍ አይደርገውም አሉ የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ።
ሃሚኒ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ “ሄዝቦላህ አሸናፊ ቡድን ነው፤ ድርጅታዊ መዋቅሩና የሰው ሃይሉም ጠንካራ ነው፤ የመሪዎቹ ግድያ ቡድኑን እንዲንበረከክ አያደርገውም” ብለዋል።
በሊባኖስ የተፈጠረውን ግጭት በማባባሱ ረገድ አሜሪካን የወቀሱት ሃሚኒ፥ ዋሽንግተን የእስራኤልን የሊባኖስ ጥቃት እቅድ አስቀድማ እንድምታውቅ ተናግረዋል።
የባይደን አስተዳደር ከህዳሩ ወር ምርጫ በፊት የቴል አቪቭን ድል እንደሚፈልግም ነው ያነሱት።
እስራኤል በሊባኖስ በሄዝቦላህ ይዞታዎች ላይ የምትፈጽመውን ድብደባ የቀጠለች ሲሆን፥ ሄዝቦላህም በሰሜናዊ እስራኤል ወታደራዊ ማዘዣዎችን ጭምር ኢላማ ያደረጉ የሚሳኤል ጥቃቶች እያደረሰ ነው።
የሊባኖስ ባለስልጣናት ከሰኞ ጀምሮ በእስራኤል የአየር ጥቃት የተገደሉ ሊባኖሳውያን ቁጥር 569 መድረሱንና ወደ ከ1 ሺህ 800 በላይ ሰዎች መቁሰላቸውን ገልጸዋል።
የኢራን ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላህ አሊ ሃሚኒ እስራኤል በጋዛም ሆነ በሊባኖስ ንጹሃንን የምትገድለው ሃማስና ሄዝቦላህን ማሸነፍ ስላልቻለች መሆኑን መግለጻቸውን ሬውተርስ ዘግቧል።
“የመጨረሻው ድል የፍልስጤምና ሊባኖስ ተዋጊዎች ነው” ያሉት ሃሚኒ፥ ቴህራን እስራኤልና ሄዝቦላህ ወደ ጦርነት ከገቡ ምን አይነት እርምጃ እንደምትወስድ ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
በመንግስታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ በትናንትናው እለት ንግግር ያደረጉት ለዘብተኛው የኢራን ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዝሽኪያን ሀገራቸው የመካከለኛው ምስራቅን በሚያተራምስ ጦርነት ውስጥ መግባት እንደማትፈልግና በጦርነቱ አንድም አሸናፊ ሃይል እንደማይኖር ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ በኒዩክሌር ፕሮግራሟ ምክንያት ቴህራን የተጣሉባትን ማዕቀቦች ለማስነሳት እንደሚሰሩ መግለጻቸውም ለሄዝቦላህ የሚደረገውን ድጋፍ ሊቀንሰው ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል።
የሄዝቦላህ እና ኢራን የምትደግፋቸው የኢራቅ ታጣቂ ቡድኖች ግን “ሄዝቦላህ እና ሊባኖስ ለኢራን ብቻ ሳይሆን በቀጠናው ለሚንቀሳቀሱ የነጻነት ተዋጊዎች ቀይ መስመር ናቸው” በሚል ቴህራን ከምዕራባውያን ጋር ግንኙነቷን ለማሻሻል በሚል ቡድኑን ገሸሽ አድርጋ እንደማትተወው ለቢቢሲ ገልጸዋል።
የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን 40 ሺህ የሃውቲ እና የኢራቅ ሽያ ፈጥኖ ደራሽ ሃይሎች በቅርቡ ወደ ሊባኖስ እንደሚገቡ ዘግበዋል።
ኢራን ሄዝቦላህ ከተመሰረተበት ከፈረንጆቹ 1982 ጀምሮ ለሊባኖሱ ቡድን ወታደራዊ እና የፋይናንስ ድጋፍ ስታደርግ መቆየቷ የሚነገር ቢሆንም በይፋ የሄዝቦላህ አጋር መሆኗን አትገልጽም።