ሊባኖስ በመካከለኛው ምስራቅ እየተፋፋመ የሚገኘውን ግጭት ማስቆም የምትችለው አሜሪካ ብቻ እንደሆነች ተናገረች
ጆ ባይደን በተመድ ጠቅላላ ጉባኤ ጦርነቱን ማስቆም የሚችል ጠንካራ እቅድ አለማቅረባቸውን የሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ተችቷል
የጸጥታው ምክር ቤት በዛሬው እለት በሂዝቦላ እና በእስራኤል መካከል በሚገኘው ውጥረት ዙርያ ይመክራል
በመከለኛው ምስራቅ እየተባባሰ የሚገኘውን የጦርነት አውድ ማስቆም የምትችለው ብቸኛዋ ሀገር አሜሪካ እንደሆነች ሊባኖስ ገልጻለች፡፡
የሀገሪቷ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አብደላህ ቦሃቢብ ዋሽንግተን በቀጠናው እና በአለም አቀፍ ደረጃ ያላት ተጽእኖ ቀጠናውን ወደ ለየለት ጦርነት ውስጥ ከመግባት የሚታደገው ነው ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በ79ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ቀጠናውን አስመልከተው ያደረጉት ንግግር “በአካባቢው ሁኔታ ላይ መፍትሄ ያላስቀመጠ ደካማ ንግግር ነው" ሲሉ ተችተውታል፡፡
ባይደን በጉባኤው ባደረጉት ንግግር ምንም እንኳን በቀጠናው የሚገኘው ውጥረት ወደ ከፍተኛ ደረጃ እየተሸጋገረ ቢሆንም ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄ ማግኝት እንደሚቻል እና የለየለት ጦርነት ለማንኛውም አካል እንደማይጠቅም ነበር የተናገሩት፡፡
እስራኤል በትላንትናው እለት በፈጸመችው የአየር ጥቃት የሂዝቦላ ሮኬት እና ሚሳይል ሀይል አዛዥ የነበረውን ኢብራሂም ኩባይሲን መግደሏን ቡድኑ አረጋግጧል፡፡
ከሰኞ ማለዳ ጀምሮ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት እስካሁን 569 ሰዎች ሲገደሉ 1835 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን የሊባኖስ ጤና ሚንስቴር መረጃ ያሳያል፡፡
በዋና ከተማዋ ቤሩት 500 ሺህ የሚጠጉ ሊባኖሳውያን በትምህርት ቤቶች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ፡፡
በመጪዎቹ ሁለት ቀናት የሊባኖሱ ጠቅላይ ሚንስትር ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በሂዝቦላ እና እስራኤል መካከል እየተባባሰ የሚገኝው ውጥረት ለአንድ አመት የቆየውን የጋዛ ጦርነት ወደ ቀጠናዊ ግጭት እንዳይለውጠው ከፍተኛ ስጋት አንዣቧል፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ብሪታንያ በሊባኖስ የሚገኙ ዜጎቿን ለማስወጣት 700 ወታደሮቿን ወደ ቆጵሮስ ልትልክ መሆኑ እየተነረ ነው፡፡
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት በዛሬው እለት በቀጠናው ስለሚገኘው የሰላም ሁኔታ የሚመክር ሲሆን የተመድ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ ሊባኖስ ሌላኛዋ ጋዝ እንድትሆን አለም አቀፉ ማህበረሰብ መፍቀድ የለበትም የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑዔል ማክሮን ከኢራኑ ፕሬዝዳንት መሱድ ፔዢሽኪን ጋር በተመድ ጉባኤ ጎን ለጎን በነበራቸው ውይይት ተሄራን የቀጠናውን ትኩሳት ለማብረድ በሂዝቦላ ላይ ተጽእኖ እንድታደርግ ጠይቀዋል፡፡
የኢራኑ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው በጋዛ ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲፈጸም እና እስራኤል በሊባኖስ እና ጋዛ እየፈጸመችው ነው ካሉት “አረመኒያዊ ተግባር” እንድትቆጠብ ጠይቀዋል፡፡