እስራኤል በኔታንያሁ ላይ ያነጣጠረ የግድያ ሴራን አከሸፍኩ አለች
በግድያ ሴራው ላይ ለመምከር ሁለት ጊዜ በኢራን ተገኝቶ ነበር የተባለ እስራኤላዊ በቁጥጥር ስር መዋሉንም አስታውቃለች
እስራኤል የሄዝቦላህን ይዞታዎችን መደብደቧን መቀጠሏ ከ18 አመት በኋላ ጦርነት እንዳይጀመር ስጋት ፈጥሯል
እስራኤል በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ሊቃጣ የነበረ የግድያ ሙከራን ማክሸፏን አስታወቀች።
የሀገሪቱ ፖሊስና የደህንነት መስሪያ ቤት (ሺን ቤት) በጋራ ባወጡት መግለጫ፥ በኢራን በሚደገፈው የግድያ ሴራ ሲሳተፍ ነበር የተባለ እስራኤላዊ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገልጸዋል።
ከቱርክ ጋር ግንኙነት አለው የተባለው እስራኤላዊ ነጋዴ መሆኑ የተነገረ ሲሆን፥ የግድያ ሴራውን በተመለከተ በኢራን በተካሄዱ ውይይቶች በጥቂቱ ሁለት ጊዜ መሳተፉን መግለጫው ጠቁሟል።
ተጠርጣሪው ኔታንያሁ፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት እና የሀገር ውስጥ የደህንነት ተቋሙ ሃላፊ የሚገደሉበትን መንገድ በተመለከተ በተደረጉ ውይይቶች ተሳትፏል ይላል መግለጫው።
ባለፈው ወር በቁጥጥር ስር የዋለውን ተጠርጣሪ ስም መግለጫው ባይጠቅስም የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን የ73 አመቱ የአሽኬሎን ከተማ ነዋሪ ሞቲ ማማን መሆኑን ዘግበዋል።
ለቢዝነስ ጉዳይ ለመምከር በቱርክ አድርጎ ወደ ኢራን እንደገባ ከቴህራን መውጣት እንደማይችል የተነገረው ተጠርጣሪው ከኢራን የደህንነት ባለስልጣናት ጋር እንዲገናኝ ተደርጎ ተልዕኮዎች እንደተሰጡት ነው ሺን ቤት የገለጸው።
ለቴህራን ገንዘብና መሳሪያዎችን ማዘዋወር፣ በእስራኤል ሰዎች በብዛት የሚገኙባቸውን አካባቢዎች ፎቶግራፍ አንስቶ መላክና ሌሎች ተልዕኮዎች ተሰጥቶት ወደ እስራኤል ቢገባም የተባለውን ሳያደርግ ዳግም ወደ ኢራን መመለሱንም ጠቅሷል።
በነሃሴ ወር ወደ ኢራን ሲመለስ የሽብር ጥቃት እንዲፈጽም አልያም የእስራኤል ባለስልጣናትን እንዲገድል ጥያቄ ቀርቦለት 1 ሚሊየን ዶላር እንዲከፈለው ጠይቆ የቴህራን ባለስልጣናት ጥያቄውን ሳይቀበሉት መቅረቱንም ነው መግለጫው ያብራራው። በግድያ ሴራ ስብሰባዎቹ በመሳተፉ ግን 5 ሺህ 570 ዶላር እንደተከፈለውም በመጥቀስ።
እስራኤል፥ በኢራን የሀገሪቱን ዜጎች ጭምር በመመልመል የስለላ ስራ የማከናወን የረጅም ጊዜ ልምድ አላት። በሀምሌ ወር የሃማስ መሪ ኢስማኤል ሃኒየህ በቴህራን መግደሏም የዚህ ማሳያ ተደርጎ ይነሳል።
ኢራንም በእስራኤል የወንጀል ታሪክ ያላቸውን ሰዎች በመመልመል ለሽብር ተልዕኮ ዝግጁ በማድረግ ላይ እንደምትገኝ የእስራኤል የሀገር ውስጥ የደህንነት ተቋም (ሺን ቤት) ገልጿል።
ተቋሙ ባለፈው ሳምንትም በቴህራን የሚደገፈው የሊባኖሱ ሄዝቦላህ የቀድሞውን የእስራኤል መከላከያ ሚኒስትር እና የጦር አዛዥ ሞሸ ያሎን ለመግደል የተጎነጎነ ሴራን ደርሼበታለው ማለቱ የሚታወስ ነው።
በተያያዘ የእስራኤል ጄቶች በዛሬው እለት በርካታ የሄዝቦላህ ይዞታዎችን ሲደበድቡ መዋላቸውን የእስራኤል መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ትናንት እና ከትናንት በስቲያ የሬዲዮ መገናኛ መሳሪያዎችን በማፈንዳት ከ30 በላይ ሊባኖሳውያን መገደላቸውና ከ3 ሺህ 200 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ይታወሳል።
እስራኤል “ፔጀር” በተሰኙት ገመድ አልባ የመገናኛ መሳሪያዎች በተፈጸሙት ጥቃቶች ዙሪያ እስካሁን አስተያየት ባትሰጥም የቤሩት እና ሄዝቦላህ አመራሮች ቴል አቪቭን ተጠያቂ አድርገዋል።
በዛሬው እለት በደቡባዊ ሊባኖስ የቀጠለው የአየር ጥቃትም እስራኤልና ሄዝቦላህ ከ18 አመት በኋላ ወደ ጦርነት ለመግባት ከጫፍ መድረሳቸውን ያመላክታል ተብሏል።