በብሪታንያ ዋና ከተማ ለንድን በአንድ ሰአት ልዩነት ውስጥ አንድ ሴት እንደምትደፈር ተነገረ
በመዲናዋ በቀን ከ8800 በላይ ሴቶች ላይ አስገድዶ መድፈር ወንጀል እንደሚፈጸም የፖሊስ መረጃ ጠቁሟል
በአለም ላይ ከሚኖሩ ሴቶች 35 በመቶዎቹ በህይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንድ ጊዜ ተገደው ይደፈራሉ
በለንደን አስገድዶ መድፈርን ጨምሮ በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጾታዊ ጥቃቶች በየአመቱ ጭማሪ እያሳዩ እንደሚገኙ ተነግሯል፡፡
የመዲናዋ ፖሊስ ይፋ ባደረገው መረጃ በ2023 በየአንድ ሰአት ልዩነት አንድ ሴት እንደምትደፈር በ24 ሰአታት ውስጥ ደግሞ 8800 ሴቶች ላይ ወንጀሉ እንደሚፈጸም ነው ያመላከተው፡፡
በ2023 የተከሰተው የአስገድዶ መድፈር ምጣኔ ባለፉት አምስት አመታት ከታየው የ14 በመቶ ጭማሪ እንደነበረው ያስታወቀው ፖሊስ በ26 ደቂቃ ልዩነት ከጾታዊ ጥቃት ጋር የተያያዘ ሪፖርት እንደሚደርሰው ገልጿል፡፡
መቀመጫውን በለንደን ያደረገው አስገድዶ መድፈርን መከላከል ላይ የሚሰራው አርሲሲ የተባለው ተቋም በዋና ከተማዋ ለንደን ህጻናትን ጨምሮ ሴቶች ላይ ያነጣጠረው ጾታዊ ጥቃት የመላ ሀገሪቱን ሁኔታ የሚያመላክት ነው ብሏል፡፡
እንደ ተቋሙ መረጃ ከሆነ በከተማዋ የአስገድዶ መድፈር ከሚፈጸምባቸው ስድስት ሴቶች መካከል ለፖሊስ የምታመለክተው አንድ ሴት ብቻ ነች፡፡
ፖሊስ በበኩሉ በ2023 ከደረሱ የአስገድዶ መድፈር ወንጀሎች 4300ዎቹ የተፈጸሙት እድሜቸው ለጾታዊ ግንኙነት ባልደረሰ ህጻናት መሆኑን ገልጿል፡፡
በህጻናት ላይ የሚደርሰው ጥቃት በአዋቂ እድሜ ላይ በሚገኙ ሰዎች እና በእድሜ እኩያዎቻቸው ጭምር የሚፈጸም ነው፡፡
በታዳጊ እድሜ ላይ የሚገኙ ህጻናት ለማህበራዊ ትስስር ገጽ እና ለወሲባዊ ፊልሞች ያላቸው መርዛማ ተጋላጭነት መጨመር ወሲባዊ ጥቃትን እንዲፈጸሙ እንደሚያነሳሳቸው ነው ፖሊስ ያስታወቀው፡፡
በ2018 በለንደን በ818 ሰዎች ላይ የጾታዊ ጥቃት ክስ ተመስርቷል። በቀጣዩ አመት ወደ 800 ዝቅ ቢልም ከ2020 ጀምሮ ከአስገድዶ መድፈር ጋር በተገኛኘ በፍርድ ቤት ክስ የሚመሰረትባቸው ሰዎች በሺዎች እንደሚቆጠሩ ተነግሯል፡፡
በአስገድዶ መድፈር ላይ የሚደረጉ የፍርድ ሂደቶች እስከ 423 ቀን ድረስ እንደሚወስዱ የሚናገሩት የሴት መብት ተሟጋቾች በህግ ሂደቱ ላይ ማስረጃ መሰረት ያደረገ አፋጣኝ ፍትህ መስጠት ወንጀሉን ለመቀነስ እንደሚረዳ ይገልጻሉ፡፡
በአለም ላይ ከሚገኙ ሴቶች 35 በመቶዎቹ ቢያንስ አንድ ጊዜ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል የሚፈጸምባቸው ሲሆን ከነዚህ መካከል ወደ ፖሊስ እና ህግ አካላት የሚሄዱት 10 በመቶዎቹ ብቻ ናቻው፡፡
በተጨማሪም የአስገድዶ መደፈር ወንጀለኛን ተጠያቂ ለማድረግ የሚወጡ ህጎች ውስብስብነት እና ተጠቂዎች ወደ ህግ አካላት የሚሄዱበት መጠን ዝቅተኛ መሆን 97 በመቶ ደፋሪዎች ተጠያቂ ሳይሆኑ እንዲቀሩ አድርጓል፡፡