ወደ ሊባኖስ በረራ ያቆሙ አየርመንገዶች የትኞቹ ናቸው?
የእስራኤልና ሄዝቦላህ ፍጥጫ የአለማችን ዋና ዋና አየርመንገዶች መነሻና መዳረሻቸውን ቤሩት ያደረጉ በረራዎችን እንዲያቋርጡ አድርጓል
የእስራኤል ጦር “ሄዝቦላህ ፋታ ሊሰጠው አይገባም፤ ጥቃቱ በሁሉም አቅጣጫ ይቀጥላል” ብሏል
እስራኤል በትናንትናው እለት በሊባኖስ በፈጸመችው የአየር ድብደባ 500 የሚጠጉ ሰዎች መሞታቸውን ተከትሎ ቤሩት ውጥረት ውስጥ ናት።
የእስራኤል ጦር በዛሬው እለት ባወጣው መግለጫ “ሄዝቦላህ ፋታ ሊሰጠው አይገባም፤ በሁሉም አቅጣጫ ዘላቂና ከባድ ጥቃት ማድረስ ይገባል” ብሏል።
ንጹሃን ሊባኖሳውያን ከጥቃት ኢላማ ውጭ እንዲሆኑ በጽሁፍ መልዕክት፣ በሬዲዮ እና በድረገጾች መልዕክት እያስተላለፍን ነው ያለው ጦሩ፥ ሊባኖሳውያን የማስጠንቀቂያ መልዕክቱን በዋዛ እንዳይመለከቱት አሳስቧል።
የሊባኖስ ሆስፒታሎችን ያጨናነቀው የእስራኤል የአየር ድብደባ ቴል አቪቭ ከ18 አመት በኋላ ከሄዝቦላህ ጋር የለየለት ጦርነት ውስጥ መግባቷ አይቀሬ መሆኑን ያመላክታል ተብሏል።
ወቅታዊው ሁኔታ ያሳሰባቸው የመካከለኛው ምስራቅ፣ አውሮፓ እና እስያ አየርመንገዶችም መነሻና መድረሻቸውን ቤሩት ያደረጉ በረራዎችን በጊዜያዊነት ማቋረጣቸውን አስታውቀዋል።
ወደ ሊባኖስ በረራ ያቆሙት አየርመንገዶች የሚከተሉት ናቸው፦
ኳታር አየርመንገድ
የኳታር አየርመንገድ የመንገደኞች ደህንነት ቅድሚያ ስለሚሰጠው ወደ ቤሩት የሚደረጉ በረራዎችን አቋርጫለሁ ብሏል። አየርመንገዱ ባወጣው መግለጫ የጸጥታ ሁኔታው ከተስተካከለ በነገው እለት ወደ ሊባኖስ በረራ ሊጀምር እንደሚችል ገልጿል።
ፍላይዱባይ
የኤምሬትሱ ፍላይዱባይም ዛሬ እና ነገ ወደ ቤሩት እንደማይበር ያስታወቀ ሲሆን፥ ትኬት የቆረጡ መንገደኞች የበረራ ጊዜያቸውን ማስተካከል አልያም ገንዘባቸው ተመላሽ ማድረግ ይችላሉ ብሏል።
ኤር ፍራንስ
የፈረንሳዩ አየርመንገድ “ኤር ፍራንስ” ወደ ሊባኖስ መዲና የሚያደርገውን በረራ እስከ ጥቅምት 1 2024 ማቋረጡን አስታውቋል።
ኤር ፍራንስ ባለፈው ሳምንት መነሻና መድረሻቸውን ቴል አቪቭ ያደረጉ በረራዎችን በጊዜያዊነት አቋርጦ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፥ በሳምንቱ መጨረሻ በረራውን ዳግም ጀምሯል።
ሉፍታንዛ
የጀርመኑ ግዙፍ አየርመንገድ ሉፍታንዛም ወደ ቤሩት የሚያደርገውን በረራ ለማቋረጥ ያሳለፈውን ውሳኔ እስከፊታችን ሃሙስ ማራዘሙን ይፋ አድርጓል። አየርመንገዱ በቀጠናዊው ውጥረት ምክንያት ዛሬ ወደ ቴል አቪቭና ቴህራን በረራዎችን አላደረገም ተብሏል።
ዴልታ አየርመንገድ
የአሜሪካው ዴልታ አየርመንገድ ወደ ቤሩት በጊዜያዊነት በረራ ያቋረጡ አየመንገዶችን ተቀላቅሏል። አየርመንገዱ ወደ እስከ ፈረንጆቹ ታህሳስ ወር መጨረሻ ድረስ ከኒውዮርክ ወደ ቴል አቪቭ በረራ እንደማያደርግም ነው ያስታወቀው።
የህንዱ “ኤር ኢንዲያ” እና የዮርዳኖሱ “ሮያል ጆርዳኒያን” አየርመንገዶች በእስራኤልና በሊባኖስ መካከል የተፈጠረው ውጥረት እንደሚያሳስባቸው በመግለጽ ወደ ቤሩት የሚደረጉ በረራዎችን አቋርጠዋል።
በወቅታዊው ሁኔታ ወደ ቴል አቪቭ እና ቴህራን የሚደረጉ በረራዎችን የሰረዙ አየርመንገዶች ውጥረቱ ከረገበ አገልግሎታቸውን በፍጥነት እንደሚጀምሩ መግለጻቸውን የቱርኩ ቲአርቲ ወርልድ አስነብቧል።