ሄዝቦላህ በቴል አቪቭ አቅራቢያ የሚገኘውን የሞሳድ ቢሮ ኢላማ ያደረገ ሮኬት መተኮሱን ገለጸ
የእስራኤል ጦር በበኩሉ ከሊባኖስ አቅጣጫ የተተኮሰ ሚሳኤልን መትቶ መጣሉን አስታውቋል
እስራኤል በሊባኖስ እየወሰደችው ባለው የተጠናከረ የአየር ድብደባ 500 ሺህ ሊባኖሳውያን መፈናቀላቸው ተገልጿል
የሊባኖሱ ሄዝቦላህ የእስራኤል የስለላ ተቋም (ሞሳድ) ዋና ቢሮን ኢላማ ያደረገ ሮኬት መተኮሱን አስታወቀ።
ዋና ቢሮው በቴል አቪቭ አቅራቢያ የሚገኘው ሞሳድ በሊባኖስ በሄዝቦላህ አባላት እጅ የነበሩ የሬዲዮ መገናኛ መሳሪያዎች ፍንዳታን ማቀነባበሩ ተነግሯል።
የቡድኑ መሪዎች በቤሩት ሲገደሉም ሞሳድ ትልቁን ድርሻ መውሰዱን የገለጸው ሄዝቦላህ የተኮሰው ሮኬት ስላደረሰው ጉዳት ያለው ነገር የለም።
የእስራኤል ጦር ግን ከሊባኖስ የተተኮሰ ምድር ለምድር ተምዘግዛጊ ሚሳኤል በአየር መቃወሚያ ተመቶ መውደቁንና እስካሁን ጉዳት ስለመድረሱ ሪፖርት አለመደረጉን ጠቅሷል።
ከሶሪያ የእስራኤልን ድንበር አቋርጦ የገባ ድሮን በጄት ተመቶ መውደቁንም ነው ጦሩ የገለጸው።
ዛሬ ማለዳ በቴል አቪቭ እና ናታንያ ከተሞች የአደጋ ማስጠንቀቂያ ድምጾች ሲሰሙ እንደነበር ሬውተርስ ዘግቧል።
በኢራን እንደሚደገፍ የሚነገርለት ሄዝቦላህ ባለፉት ቀናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሚሳኤሎችና ሮኬቶችን ወደ እስራኤል ተኩሷል።
የእስራኤል ጦርም በዚህ ሳምንት በሊባኖስ ከ18 አመት በኋላ መጠነሰፊ የሆነ የአየር ጥቃት በማድረስ ላይ ይገኛል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የሄዝቦላህ ይዞታዎችን ደብድቤያለሁ ያለችው ቴል አቪቭ፥ የቡድኑን የሚሳኤል እና ሮኬት ሃይል መሪ ኢብራሂም ቁባይሲን በቤሩት መግደሏ የሚታወስ ነው።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮቭ ጋላንት በሄዝቦላህ ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ቡድኑን ማዳከሙንና ድብደባው የእስራኤል የደህንነት ስጋት መሆኑ እስኪያቆም ድረስ ይቀጥላል ማለታቸው ተዘግቧል።
እስራኤል ከሰኞ ማለዳ ጀምሮ በፈጸመችው ድብደባ የተገደሉ ሊባኖሳውያን ቁጥር 569 መድረሱን የጠቀሱት የሊባኖስ የጤና ሚኒስትር ፊራስ አቢያድ፥ 1 ሺህ 835 ሰዎችም መቁሰላቸውን አብራርተዋል።
የሊባኖስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አብደላህ ቡኣ ሃቢብ በበኩላቸው ከ500 ሺህ በላይ ሊባኖሳውያን መፈናቀላቸውንና የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በቀጣይ ሁለት ቀናት ከአሜሪካ ባለስልጣናት ጋር እንደገናኙ ተናግረዋል።
የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “ሊባኖስ የጦርነት ቋፍ ውስጥ ናት፣ የሊባኖስ፣ የእስራኤልም ሆነ የመላው አለም ህዝብ ሊባኖስ ሌላኛዋ ጋዛ እንድትሆን መፍቀድ የለበትም” ብለዋል።
የጸጥታው ምክርቤትም ከ18 አመት በኋላ ወደለየለት ጦርነት ለመግባት በተቃረቡት እስራኤልና ሄዝቦላህ ወቅታዊ ግጭት ዙሪያ በዛሬው እለት ይመክራል ተብሏል።