የእስራኤል ጦር በፈጸመው ጥቃት በሊባኖስ ድንበር የምትገኝን መንደር ማውደሙ ተነገረ
የከተማዋ ከንቲባ ሞሀመድ ስሩር ከተማዋ መጠገን በማትችልበት ደረጃ ዙሪያ ገባዋ ተመትቷል ብለዋል
በእስራኤል እና በኢራን እንደሚደገፍ በሚገለጸው የሄዝቦላ ታጣቂ መካከል ያለው ግጭት ጋብ ያለ ቢሆንም በ18 አመታት ውስጥ ከፍተኛ የተባለ ፍጥጫ አስከትሏል
የእስራኤል ጦር ለወራት በፈጸማቸው ተከታታይ የቦምብ ጥቃቶች አይታ አል ሻብ የተባለችውን የሊባኖስ መንደር ማውደሙን የሚያሳይ የሳተላይት ምስል ወጥቷል።
ፕላኔት ላብ ፒቢሲ በተባለው የግል የሳተላይት ኦፐሬተር የተነሳውን ምስል መገምገሙን የገለጸው ሮይተርስ በአይታ አል ሻብ ቢያንስ 64 የወደሙ ቦታዎች መኖራቸውን ዘግቧል። እነዚህ ቦታዎች ከአንድ በላይ ህንጻዎች ያሉባቸው ናቸው።
በደቡብ ሊባኖስ የምትገኘው እና ሄዝቦላ ከሺያ ሙስሊሞች ከፍተኛ ድጋፍ የሚያገኝባት አይታ አል ሻብ፣ በፈረንጆቹ 2006 እስራኤል አጠቃላይ ጦርነት በከፈተችበት ወቅት ጥቃቱን የመከተባት ከተማ ነች።
በእስራኤል እና በኢራን እንደሚደገፍ በሚገለጸው የሄዝቦላ ታጣቂ መካከል ያለው ግጭት ጋብ ያለ ቢሆንም በ18 አመታት ውስጥ ከፍተኛ የተባለ ፍጥጫ አስከትሏል። እስራኤል እና ሄዝቦላ ባደረጉት የተኩስ ልውውጥ በሰሜን እስራኤል እና በደቡባዊ ሊባኖስ ህንጻዎች እና የእርሻ ቦታዎች ወድመዋል።
ሁለቱ አካላት የተኩስ ልውውጥ የጀመሩት የፍልስጤም ታጣቂ ቡድን ሀማስ ባለፈው ጥቅምት ወር በእስራኤል ላይ ከባድ የተባለ ጥቃት ካደረሰ በኋላ ነው።
ግጭቱ በሁለቱም በኩል በድንበር አካበቢ ያለው ነዋሪ ህዝብ እንዲቀንስ እና በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ አድርጓቸዋል።
በአይታ አል ሻብ የደረሰው ውድመት ከተማዋ በ2006 በነበረው ጦርነት ወቅት ከደረሰባት ገዳት ጋር ያነጻጸሩት መኖራቸውን የገለጸው ሮይተርስ ውጥረቱ አሁንም አጠቃላይ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል ብሏል።
እስራኤል ከሊባኖስ በኩል በተፈጸመው ጥቃት 18 ወታደሮች እና 10 ንጹሀን መገደላቸውን ገልጻለች። በሊባኖስ በኩል ደግሞ 300 የሄዝቦላ ተዋጊዎች እና 87 ንጹሀን መገደላቸውን ባሰባሰበው መረጃ ለማወቅ መቻሉን ሮይተርስ ጠቅሷል።
ከእስራኤል ድንበር በአንድ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ይች ከተማ በከፍተኛ ደረጃ መመታቷን የደቡብ ሊባኖስ ልማት ኃላፊ ኤጀንሲ ሀሽም ሀይደር ለሮይተርስ ተናግሯል።
የከተማዋ ከንቲባ ሞሀመድ ስሩርም ከተማዋ መጠገን በማትችልበት ደረጃ ዙሪያ ገባዋ ተመትቷል ብለዋል።
የአሁኑ ግጭት የተጀመረው ከጥቅቱ የሀማስ ጥቃት ማግስት ነው። ሄዝቦላ ወደ እስራኤል የተኮሰው ለሀማስ አጋርነት ለማሳየት መሆኑን እና ጥቃቱን የሚያቆመውም የጋዛው ጦርነት ሲቆም እንደሆነ መግለጹ ይታወሳል።
በቅርቡ እስራኤል በሄዝቦላ ላይ በእግረኛ ጦር ለመዝመት ዝግጅት ማድረጓን ገለጻ ነበር። ይህን ተከትሎ ሄዝቦላ እስራኤል ከሞከረችው ከፍተኛ ኪሳራ ይገጥማታል ሲል አስጠንቅቋል።