በእስራኤል ሃማስ ጦርነት የሞቱ ፍሊስጤማውያን ቁጥር ከ37 ሺህ 400 ተሻግሯል
የእስራኤል ጦር በ24 ሰዓታት ውስጥ በጋዛ ሰርጥ በተፈጸማቸው ጥቃቶች ከ100 በላይ ፍሊስጤማውያን መገደላቸውን በሃማስ የሚመራው መንግስት ባለስልጣናት አስታወቀዋል።
የእስራኤል ጦር አዳሩን በጋዛ ሰርጥ በፈጸመው ጥቃት ቢያንስ 42 ፍሊስጤማውያን መሞታቸውንም ነው በሃማስ የሚመራው መንግስት መገናኛ ብዙሃን የዘገቡት።
የእስራኤል ጦር የአየር ድብደባ ከፈጸመባቸው ቦታዎች መካከል በጋዛ ሰርጥ ውስጥ ከሚገኙ ታሪካዊ የስደተኞች መጠለያ መካከል አል አሻ የሚገኙ ቤቶች ሲሆኑ፤ በዚህ ስፍራ 24 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል።
ሌላኛው የእስራኤል ጦር ኢላማ የነበረው በአል ቱፋህ የሚገኘው መኖሪያ ቤቶች አካባቢ ላይ ሲሆን፤ በዚህ ስፍራም 18 ሰዎች መሞታቸው ነው የተገለጸው።
የእስራኤል ጦር ጥቃቱን ተከትሎ ባወጣው መግለጫው፤ የእስራኤል መከላከያ ኃይሎች በሁለት የሃማስ ኢላማዎች ላይ ጥቃት መሰንዘሩን እና በዚህም የሃማስ ወታደራዊ ኢላማዎችን ማውደሙን አስታውቋል።
በሃማስ ወታደራዊ መሰረተ ልማቶችን ላይ በተፈጸመው የአየር ድብደባ ዙሪያ ዝርዝር መረጃ በቅርቡ እለቃለሁም ብሏል የእስራኤል ጦር በመግለጫው።
ሃማስ በበኩሉ ባወጣው መግለጫ የእስራኤል ጦር መታደራዊ መሰረት ልማቶቹን ስለ መምታቱ ያለው ነገር የለም።
ሃማስ በመግለጫው የእስራኤል ጦር ንጹሃንን ኢማላማ አድርጎ ጥቃት መፈጸሙን በመግለጽ፤ “ወራሪዎችና እና የናዚ መሪዎቻቸው ንጹሃንን ኢላማ ማድረጋቸው ዋጋ ያስከፍላቸዋል” ብሏል
እስራኤል በጋዛ ሰርጥ የአየር እና የምድር ጦር ዘመቻ የጀመረችው ሃማስ ጥቅምት 7 በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት በመፈጸም 1 ሺህ 200 ሰዎችን መግደሉንና፤ 250 ሰዎችን ማገቱን ተከትሎ ነው።
ይህንን ተከትሎም እስራኤል በጋዛ እየወሰደችው ባለው እርምጃ ከ37 ሺህ 400 በላይ ፍሊስጤማውያን የሞቱ ሲሆን፤ ከእነዚህም መካከል 100 ሰዎች ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ነው የተገደሉት።