ቱርክ ከእስራኤል ጋር ውጥረት ውስጥ ከገባችው ሊባኖስ ጎን እንደምትቆም ኢርዶጋን ተናገሩ
ኢርዶጋን ሌሎች የቀጣናው ሀገራትም ከቤሩት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል
ቱርክ እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለውን ዘመቻ በጽኑ ከሚያወግዙ ሀገራት አንዷ ነች
ቱርክ ከእስራኤል ጋር ውጥረት ውስጥ ከገባችው ሊባኖስ ጎን እንደምትቆም ኢርዶጋን ተናገሩ።
በእስራኤል እና ሊባኖስ መካከል ያለው ውጥረት ባየለበት ወቅት፣ የቱርኩ ፕሬዝደንት ታይፕ ኢርዶጋን ቱርክ ከሊባኖስ ጎን እንደምትቆም ተናግረዋል።
ኢርዶጋን ሌሎች የቀጣናው ሀገራትም ከቤሩት ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል።
በላፉት ሳምንታት በእስራኤል እና ሊባኖስ ድንበር አካባቢ ያለው ውጥረት መጨመረ ቀጣናዊ ግጭት ይነሳል የሚለውን ስጋት ከፍ አድርጎታል።
በድንበር አካባባቢ ያሉ ግጭቶች በሁለቱም በኩል በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆኗል።ፕሬዝደንቱ ለኤኬ ፓርቲ የፓርላማ አባላት በሳሙት ንግግር የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ጦርነቱን ወደቀጣናው ለማዘመት አቅደዋል ሲሉ ከሰዋል።
"እስራኤል ጋዛን ካቃጠለች እና ካወደመች በኋላ አሁን ላይ አይኗን ወደ ሊባኖሰ ያዞረች ይመስላል። ምዕራባውያን ሀገራትም ከመጋረጃ ጀርባ ሆነው እስራኤልን እየረዷት ነው" ያሉት ኢርዶጋን ምዕራባዊያን ለእስራኤል የሚያደርጉት ድጋፍ ደስ የማይል ነው ብለዋል።
"ቱርክ ከወንድም የሊባኖስ ህዝብ እና መንግስት ጋር ትቆማለች። በቀጣናው ያሉ ሌሎች ሀገራትም ለሊባኖስ አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ እጠይቃለሁ" ብለዋል ኢርዶጋን።
የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሀካን ፊደን ከሳምንት በፊት በእስራኤል እና ሊባኖስ ውጥረት ጉዳይ አስተያየት በሰጡበት ወቅት የቱርክ መንግስት ግጭቱ ይስፋፋል የሚል ስጋት እንዳለው ገልጸዋል።
ፊዳን ለሊባኖስ በቅርብ ርቀት የምትገኘውን የአውሮፓ ህብረት አባሏን ሲፕረስን ከግጭቱ ራሷን እንድታርቅ አሳስበዋል።
ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የቱርክ የደህንነት መረጃ ሲፕረስ በጋዛ ላይ የቅኝት በረራ ለሚያደርጉ የተወሰኑ ሀገራት እንደጦር ሰፈር እያገለገለች መሆኗን ያሳያል ብለዋል።
ሲፕረስ ግን በምንም መልኩ በጦርነቱ እንደማትሳተፍ እየገለጸች ነው።ሲፕለረስ ሊባኖስ ከአውሮፓ ህብረት ድጋፍ እንድታገኝ ማግባባቷ እና እርዳታ ወደ ጋዛ እንዲገባ የማሪታይም መተላለፊያ ማቋቋሟ ተገልጿል።
ቱርክ እስራኤል በጋዛ እያካሄደች ያለውን ዘመቻ በጽኑ ከሚያወግዙ ሀገራት አንዷ ነች።