ቲክቶክን ሊተካ ይችላል የሚባለው "ሌመን8" መተግበሪያ ማን ነው?
ቲክቶክ በአሜሪካ ሊታገድ ይችላል መባሉን ተከትሎ "ሌመን8" መተግበሪያን እያስተዋወቀ ይገኛል
ሌመን8 መተግበሪያ ከሚሊኒየም በኋላ የተወለዱ ወጣቶችን ለመሳብ ተብሎ ዩለማ መተግበሪያ ነው
ቲክቶክን ሊተካ ይችላል የሚባለው "ሌመን8" መተግበሪያ ማን ነው?
መሰረቱን በቻይን ያደረገው እና ባይት ዳንስ ኩባንያ የተመሰረተው ቲክቶክ በአሜሪካ የደህንነት ስጋት ደቅኗል በሚል እንደሚታገድ ከወራት በፊት ውሳኔ ተላልፎበት ነበር።
አጫጭር ምስሎችን በማሰራጨት የሚታወቀው ቲክቶክ በአሜሪካ ብቻ ከ170 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችን አፍርቷል።
ይህ የማህበራዊ ትስስር መተግበሪያ የአሜሪካዊያን ተቋማት እና ዜጎችን መረጃዎች ለቻይና አሳልፎ እየሰጠ ነው የሚል ቅሬታ ሲቀርብበት ቆይቷል።
ይህን ተከትሎ የፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አስተዳድር ቲክቶክ ብሔራዊ የደህንነት ስጋት ደቅኗል በሚል ለአሜሪካዊያን ኩባንያዎች እንዲሸጥ አልያም እንዲታገድ በሚል ውሳኔ ተላልፎበታል።
ህጉ የሚተገበር ከሆነ ቲክቶክ በአሜሪካ ምድር ሊዘጋ ሁለት ሳምንት ብቻ ይቀረዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን ባይት ዳንስ ኩባንያ ሌመን8 የተሰኘ የማህበራዊ ትስስር መተግበሪያን አስቀድሞ ለቲክቶክ ተጠቃሚዎቹ እያስተዋወቀ ይገኛል።
ሌመን8 መተግበሪያ በቲክቶክ እናት ኩባንያ ባይት ዳንስ ስር ያለ ሲሆን አሁን ላይ በትንሹ በቀን አንድ ሚሊዮን ተጠቃሚዎች አሉት።
ኩባንያው እንደገለጸው ከሆነ ከሁለት ሺህ ሚሊኒየም በኋላ የተወለዱ ወጣቶችን ወይም የዜድ ትውልድን ለመያዝ ታስቦ የለማ ነው።
መተግበሪያው ለመጀመሪያ ጊዜ በጃፓን ከአምስት ዓመት በፊት ይፋ የተደረገ ሲሆን በለንደን እና አሜሪካ ቢሮዎች አሉት።
ዩሮ ኒውስ በቴክኖሎጂ አምዱ እንደዘገበው ከሆነ ሌመን8 መተግበሪያ ቁንክና፣ ፋሽን፣ ምግብ ማብሰል፣ ጉዞዎች እና ከእንስሳት ህይወት ጋር የተያያዙ ይዘቶች በብዛት ይሰራጩበታል።
የፒንትረስት፣ ኢንስታግራም እና ቲክቶክን ለመገዳደር ተብሎ እንደለማም ተገልጿል።
ባይት ዳንስ ኩባንያ በአሜሪካ ቲክቶክ ከታገደ ከ170 ሚሊዮን በላይ ደንበኞቹ ወደ ሌመን8 እንዲዛወሩ ሊያደርግ ይችላልም ተብሏል።