አትሌት ስለሺ ስህን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመረጠ
ስለሺ ስህን ከተሰጠ 26 ድምፅ መካከል 11 ድምፅ በማግኘት ነው የተመረጠው
28ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ዛሬ ተካሂዷል
አትሌት ስለሺ ስህን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ መመረጡ ተገለጸ።
28ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤ ኮማንደር አትሌት ስለሺ ስህን ፕሬዚዳንት አድርጎ መምረጡን ፌዴሬሽኑ አስታውቋል።
አትሌት ስለሺ ስህን ከተሰጠው አጠቃላይ 26 ድምፅ መካከል 11 ድምፅ በማግኘት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሆኖ ተመጧል።
በምርጫው ውጤት መሰረትም
1. አትሌት ስለሺ ስህን ከኦሮሚያ 11 ድምጽ
2.አትሌት ገብረእግዚአብሄር ገ/ማሪያም ከትግራይ ክልል 9 ድምጽ
3.አቶ ያየህ አዲስ ከአማራ ክልል 4 ድምጽ
4 ሪሳል ኦፒዮ ከጋምቤላ ክልል 1 ድምጽ
5.ኮማንደር ግርማ ዳባ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 1 ድምጽ
6 አቶ ዱቤ ጂሎ ከአዲስ አበባ 0 ድምጽ አግኝተዋል።
ይህንን ተከትሎም አትሌት ስለሺ ለቀጣይ አራት አመት ረዳት ኮሚሽነር ደራርቱ ቱሉን በመተካት ፌዴሬሽኑን በፕሬዚዳንትነት እንደሚመራም ታውቋል።
አትሌት ስለሺ በመካከለኛ ርቀት 3 ሺሕ ሜትር፣ በረጅም ርቀት 5 ሺሕ እና 10 ሺሕ ሜትር፤ በ10፣ 15 እና 20 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫዎች፤ በሀገር አቋራጭ፤ በግማሽ ማራቶንና በማራቶን ውድድሮች ከ15 ዓመታት በላይ ተወዳድሯል፡፡
አትሌት ስለሺ ከእነ አበበ ቢቂላ፣ ማሞ ወልዴና ምሩፅ ይፍጠር በኋላ በዓለም አትሌቲክስ ፍፁም የበላይነት የነበረው የአረንጓዴው ጎርፍ ትውልድን ከነ ኃይሌ ገብረስላሴ እና ቀነኒሳ በቀለ ጋር በመሆን ገንብቷል፡፡
አትሌቱ ካለው የረጀም ጊዜ የአትሌቲክስ ውድድር ልምድ እና ግለሰባዊ ስነ-ምግባር አንፃር የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ያጋጠመውን ስብራት በመጠገን ወደ ቀድሞው ገናናቱ ይመልሰዋል ተብሎ ታምኖበታል፡፡