ሩሲያ ወደ ዩክሬን አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል መተኮሷ ተነገረ
የዩክሬን አየር ሃይል ሞስኮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተኮሰችውና 700 ኪሎሜትር የተጓዘው ባለስቲክ ሚሳኤል የዲኒፕሮ ከተማን ኢላማ ማድረጉን ገልጿል
ኬቭ ከአሜሪካና ብሪታንያ በተላኩላት ሚሳኤሎች ሩሲያ ላይ ጥቃት ማድረስ መጀመሯ ሞስኮን አስቆጥቷል
ሩሲያ ወደ ዩክሬን ለመጀመሪያ ጊዜ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል መተኮሷን የዩክሬን አየርሃይል አስታወቀ።
አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤሉ በዲኒፕሮ ከተማ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኙ "ወሳኝ መሰረተልማቶችን" ኢላማ አድርጓል ያለው የዩክሬን አየር ሃይል፥ ስለሚሳኤሉ አይነትም ሆነ ስላደረሰው ጉዳት ማብራሪያ አልሰጠም።
የዲኒፕሮ ግዛት አስተዳዳሪ ሰሂይ ሊሳክ ግን ሚሳኤሉ በኢንዱስትሪ ላይ የእሳት ቃጠሎ ማስነሳቱንና ሁለት ሰዎች መጎዳታቸውን መናገራቸው ሬውተርስ ዘግቧል።
33ኛ ወሩን በያዘው የዩክሬን ጦርነት ሩሲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ተጠቅማዋለች የተባለው አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል የኒዩክሌር አረር መሸከም የሚችል ነው።
የክሬምሊን ቃልአቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ የዩክሬን አየርሃይል ስላቀረበው መረጃ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ የመከላከያ ሚኒስቴርን ጠይቁ የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።
ሩሲያ በርግጥም ወደ ዩክሬን አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ከተኮሰች ሚሳኤሉ ለወታደራዊ አገልግሎት ሲውል የመጀመሪያው ይሆናል።
ተቀማጭነቱን ኬቭ ያደረገው ዩክሬንስካ ፕራቫዳ የተሰኘ የመገናኛ ብዙሃን ስማቸው ያልተጠቀሰ ምንጮቹን ጠቅሶ እንዳስነበበው ዛሬ ወደ ዩክሬን የተተኮሰው የሩሲያ አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል "አርኤስ-26" የሚል መጠሪያ ያለው ነው።
"አርኤስ-26" በጠጣር ነዳጅ የሚሰራ ሲሆን እስከ 5 ሺህ 800 ኪሎሜትሮች ድረስ በመምዘግዘግ ኢላማውን ይመታል።
ከ12 አመት በፊት ስኬታማ ሙከራ ያደረገው "አርኤስ-26" 12 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ክብደቱ 36 ቶን እንደሆነ የስትራቴጂክና አለማቀፍ ጉዳዮች ጥናት ማዕከል (ሲኤስአይኤስ) መረጃ ያሳያል።
ሚሳኤሉ እስከ 800 ኪሎግራም የሚመዝን የኒዩክሌር አረር መሸከም እንደሚችልም ተገልጿል።
ሩሲያ ወደ ዩክሬን አህጉር አቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል መተኮሷን ባታረጋግጥም ኬቭ ከአሜሪካ እና ብሪታንያ በተላኩላት የረጅም ርቀት ሚሳኤሎች ጥቃት ማድረስ መጀመሯ ከባድ ዋጋ እንደሚያስከፍል ስትዝት ቆይታለች።
ሞስኮ በዛሬው እለት ኪንዝሃል ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤል እና ሰባት "ኬኤች-101" ክሩዝ ሚሳኤሎች ወደ ዩክሬን መተኮሷም ቁጣዋን የገለጸችበት ነው ተብሏል።
በዩክሬኑ ጦርነት ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል የተባለው የሩሲያ አህጉርአቋራጭ ባለስቲክ ሚሳኤል ከዩክሬኗ ዲኒፕሮ ከተማ በ700 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ከሚገኘው አስትራካን ክልል መተኮሱ እየተዘገበ ነው።
ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዩክሬን ከአሜሪካ እና ሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት በተሰጧት ሚሳኤሎች በሩሲያ ግዛት ውስጥ ጥቃት ከከፈተች "የኔቶ አባል ሀገራት ከሩሲያ ጋር በቀጥታ ጦርነት እንደጀመሩ ይቆጠራል፤ የኒዩክሌር ጦርነትንም ሊቀሰቅስ ይችላል" ሲሉ ማስጠንቀቃቸው የሚታወስ ነው።