ትራምፕ ቲክቶክ አሜሪካ ውስጥ የተወሰነ ጊዜ ሳይዘጋ እንዲቆይ ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ገለጹ
ትራምፕ ወግአጥባቂ ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት በአሪዞና ፎኒክ የሰጡት አስተያየት ቲክቶክ ከአሜሪካ ገበያ እንዲወጣ እንደማይፈልጉ የሚያሳይ ነው ተብሏል
የአሜሪካ ሴኔት ቲክቶክ የብሔራዊ ደህንነት አደጋ መደቀኑን በመጥቀስ ነበር መተግበሪያው በአሜሪካ ውስጥ እንዲሸጥ ወይም አንዲታገድ የወሰነው
ትራምፕ ቲክቶክ አሜሪካ ውስጥ የተወሰነ ጊዜ ሳይዘጋ እንዲቆይ ማድረግ አስፈላጊ ሊሆን እንደሚችል ገለጹ።
የምርጫ ቅስቀሳ በሚያካሂዱበት ወቅት በቲክቶክ በቢሊዮን የሚቆጠር እይታ ማግኘታቸውን የገለጹት ተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ሳይዘጋ ለተወሰነ ጊዜ እንዲቆይ እንደሚፈልጉ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ትራምፕ ወግአጥባቂ ደጋፊዎቻቸው በተገኙበት በአሪዞና ፎኒክ የሰጡት አስተያየት ቲክቶክ ከአሜሪካ ገበያ እንዲወጣ እንደማይፈልጉ የሚያሳይ ነው ተብሏል።
የአሜሪካ ሴኔት ባለፈው ሚያዝያ ወር ቲክቶክ የብሔራዊ ደህንነት አደጋ መደቀኑን በመጥቀስ ነበር ንብረትነቱ የቻይናው ባይቲዳንስ የሆነውን መተግበሪያ በአሜሪካ ውስጥ እንዲሸጥ ወይም አንዲታገድ የወሰነው።
የቲክቶክ ባለቤቶች ጉዳዩ በህግ እንዲታይላቸው የሚፈልጉ ሲሆን የአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤትም ጉዳዩን ለመስማት ፍቃደኛ ሆኗል። ነገርግን ፍርድ ቤቱ ባይቲዳንስ የሚፈልገውን ውሳኔ ከላሳለፈ እና የድርሻ ሽያጭ የማይከናወን ከሆነ መተግበሪያው ትራምፕ በዓለ ሲመት ከመፈጸማቸው በፊት በጥር 19፣2025 አሜሪካ ውስጥ ሊታገድ ይችላል።
ትራምፕ ሴኔቱ በአብላጫ ድምጽ ቲክቶክ እንዲሸጥ ያሳላፈውን ውሳኔ እንዴት እንደሚቀለብሱት ግልጽ አይደለም።
"ማሰብ ያለብን ይመስለኛል፤ ምክንያቱም እንደምታውቀት ቲክቶክ በምንጠቀምበት ወቅት በቢሊዮኖች በመታየት በጣም ጥሩ የሚባል ምላሽ አግኝተንበታል" ሲሉ ትራምፕ "አሜሪካ ፈርስት" ለሚሉት ወግአጥባቂ ደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።
ትራምፕ ከቲክቶክ ዋና ስራ አስፈጻሚ ጋር ተገናኝተዋል።ትራምፕ በተመሳሳይ ቀን በሰጡት መግለጫ በቲክቶክ የተሳካ የምርጫ ዘመቻ ማካሄዳቸውን ተናግረዋል።
የአሜሪካ የፍትህ መስሪያ ቤት የቻይናው ቴክቶክ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት ደቅኗል ሲል ይከራከራል። ይህ የፍትህ መስሪያ ቤቱ አቋም በአብዛኞቹ የአሜሪካ የምክር ቤት አባላት የሚደገፍ ነው።
ቴክቶክ የፍትህ መስሪያ ቤቱ የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያውን ከቻይና ጋር እንደሚገናኝ መግለጹ ስህተት ነው፤ የተጠቃሚዎች መረጃ የሚከማቸው ኦራክል ኮርፖሬሽን በሚንቀሳቀሰው ክላውድ ሰርቨር አሜሪካ ውስጥ ነው ብሏል። ቲክቶክ አክሎም እንደገለጸው በአሜሪካ ተጠቃሚዎች ላይ ተጽዕኖ በሚያሳድሩ ይዘቶች ላይ ቁጥጥር የሚደረገውም አሜሪካ ውስጥ መሆኑን ገልጿል።