በሙከራ ላይ የነበሩ የኤችአይቪ ኤድስ መድሃኒቶች ምን ላይ ናቸው?
ሌናካፓቪር የተሰኘው የኤችአይቪ ኤድስ መከላከያ መድሃኒት የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራውን አጠናቋል ተብሏል

በዓለማችን ላይ 40 ሚሊዮን ገደማ ዜጎች ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ናቸው
በሙከራ ላይ የነበሩ የኤችአይቪ ኤድስ መድሃኒቶች ምን ላይ ናቸው?
የሚሊዮን ዜጎችን ህይወት የቀጠፈው ኤችአይቪ ኤድስ በሽታ እስካሁን ፈዋሽ መድሃኒት ያልተገኘለት ሲሆን የዓለም ጤና ድርጅት ለቫይረሱ መድሃኒት ለማግኘት የተለያዩ ጥረቶችን በማድረግ ላይ ነው፡፡
ከአምስት ዓመት በኋላ ማለትም በ2030 የቫይረሱን ወረርሽኝ የማጥፋት እቅድ ያስቀመጠ ሲሆን ለዚህ የሚረዱ የተለያዩ ሙከራዎች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡
ከሰሞኑ የጤና ግኝቶች ይፋ በሚደረጉበት ላንሴት የህክምና ጥናት ማዕከል ላይ በወጣው መረጃ መሰረት ሌናካፓቪር የተሰኘው መድሃኒት የመጀመሪያ ሙከራውን በስኬት አጠናቋል ተብሏል፡፡
ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች በሰውነታቸው የነበረው የኤችአይቪ ቫይረስ እንዳይራባ ማድረግ ችሏል የተባለ ሲሆን ከሌሎቹ እና በሙከራ ላይ ካሉት ክትባቶች ውጤታማ እንደሆነ ቢቢሲ በጤና አምዱ አስነብቧል፡፡
ለቫይረሱ ከፍተኛ ተጋላጭ የሆኑ ሰዎች በእንክብል መልኩ መድሃኒቱን እየወሰዱ ውጤታማ ሆነዋል የተባለ ሲሆን በክትባት መልኩ እንዲሰጥ መደረጉ ደግሞ ብዙ ጥቅም ሊኖረው ይችላልም ተብሏል፡፡
የክትባቱን ውጤታማነት ለመለካት ሲባልም በሰዎች ላይ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው በተደረገው ሙከራም ቫይረሱ በሌለባቸው 40 ሰዎች ላይ ተሞክሮ ጉዳት እንደሌለው መረጋገጡም ተገልጿል፡፡
የዚህ ክትባት ይዘት በሰዎቹ ውስጥ ከ56 ሳምንት በኋላም እንዳለ ማወቅ ተችሏል የተባለ ሲሆን በረጅም ጊዜ ውስጥ የጎንዮሽ ጉዳት እንዳለው እና እንደሌለው ተጨማሪ ምርመራዎች ይካሄዳሉ ተብሏል፡፡
መድሃኒቱ ከክትባት ይልቅ በየዕለቱ በእንክብል መልኩ ሲወሰድ የተሻለ ውጤታማ ነው የተባለ ሲሆን ይህ ግን አድካሚ እና ሊረሳ መቻሉ ስጋትን ደቅኗል፡፡
ይህን ለማስቀረት ሲባልም በየሁለት ወሩ አንዴ በክትባት መልክ መሰጠት የተጀመረ ሲሆን ይህን በዓመት አንዴ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ውጤታማ ሆኗል ተብሏል፡፡
በክትባቱ ውጤታማነት እና የጎንዩሽ ጉዳቶች ዙሪያ ተጨማሪ ምርምሮች እንደሚደረጉ ተገልጿል፡፡
ሀገራት ይህን መድሃኒት ዜጎቻቸው እንዲጠቀሙት ፈቃድ እየሰጡ ሲሆን ብሪታንያ መድሃኒቱ በሀገሯ ጥቅም ላይ ከመዋሉ በፊት ምርመራ በማድረግ ላይ ትገኛለች፡፡