ሰንሌንካ አዲሱ ኤችአይቪ ኤድስ ፈዋሽ ክትባት?......
ክትባቱ በ5ሺህ በጎ ፈቃደኛ ሰዎች ላይ ተሞክሮ ከቫይረሱ ነጻ ሆነዋል ተብሏል
አዲሱ ክትባት የፈዋሽነት ፈቃድ ለማግኘት የመጨረሻው ደረጃ ላይ እንደሆነ ተገልጿል
ኤችአይቪ ኤድስ በዓለማችን በየዓመቱ በርካታ ዜጎችን ከሚገድሉ በሽታዎች መካከል አንዱ ነው፡፡
እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ አሁን ላይ በየዓመቱ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ዜጎች በቫይረሱ የሚያዙ ሲሆን 600 ሺህ ያህል ሰዎች ደግሞ በየዓመቱ ይሞታሉ፡፡
ይህ ገዳይ ቫይረስ እስካሁን በፈዋሽነቱ የተረጋገጠ መድሃኒት ያልተገኘለት ሲሆን በርካታ ተቋማት ፈዋሽ መድሃኒት ለማግኘት የተለያዩ ምርምሮችን በማድረግ ላይ ናቸው፡፡
መቀመጫውን አሜሪካ ያደረገው ጊሊድ የተሰኘው ኩባንያ በቅርቡ ያስተዋወቀው ሰንሌንካ የተሰኘ ክትባት ከቫይረሱ በመፈወስ ረገድ ውጤታማ ሆኖ መገኘቱን ዩሮ ኒውስ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ይህ በክትባት መልክ የተመረተው መድሃኒት ቫይረሱ ባለባቸው አምስት ሺህ በጎ ፈቃደኞች ላይ ተሞክሮ ውጤታማ ሆኗል ተብሏል፡፡
በደቡብ አፍሪካ ደርባን የኤችአይቪ ኤድስ ጥናት ማዕከል አማካኝነት በተካሄደው ምርምር ክትባቱን በሁለት ዙር የወሰዱ አምስት ሺህ በጎ ፈቃደኞች ከቫይረሱ ነጻ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
በደቡብ አፍሪካ እና ኡጋንዳ ባሉ ሴቶች ላይ የተሞከረው ይህ የኤችአይቪ ኤድስ ክትባት ለሙከራ በወሰዱት ላይ አዲስ ተጠቂ አልተገኘም ተብሏል፡፡
ይሁንና በእንክብል መልኩ ከወሰዱ ተመሳሳይ በጎ ፈቃደኞች ውስጥ በሁለቱ ውስጥ ቫይረሱ እንደተገኘባቸው ተገልጿል፡፡
የደቡብ አፍሪካ ኤችአይቪ ኤድስ ጥናት ማዕከል ዳይሬክተር ሳሊም አብዱልከሪም እንዳሉት "በኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ መከላከል ዙሪያ የተገኘው ውጤት አስገራሚ ነው" ብለዋል፡፡
ሰንሌንካ የተሰኘው ይህ ክትባት በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ ካናዳ እና ሌሎችም ሀገራት በኤችአይቪ ኤድስ ፈዋሽነት ሳይሆን ለህክምና እንዲውል ፈቃድ አግኝቷል፡፡
በክትባት መልክ የሚሰጠው ይህ መድሃኒት የቫይረሱን አቅም ለማዳከም በየዕለቱ እንክብል መድሃኒት የሚወስዱ ታማሚዎችን ከመገለል ይጠብቃቸዋልም ተብሏል፡፡
የኤችአይቪ ኤድስ ፈዋሽ መድሃኒት የማግኘቱ ጉዳይ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ ደርሷል የተባለ ሲሆን ችግሩ መድሃኒቱ ውድ መሆኑ የወቅቱ ችግር እንደሚሆን ተገልጿል፡፡
ኤች አይ ቪ ኤድስ ቫይረስን ከሰውነት ውስጥ ማስወገድ መቻላቸውን ተመራማሪዎች ተናገሩ
አሁን ላይ ሰንሌንካ የተሰኘው ክትባት መድሃኒት 40 ሺህ ዶላር ሲሆን መድሃኒቱ ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆን እና ኩባንያው የዋጋ ማስተካካያ እንዲያደርግ አማራጮች በመፈለግ ላይ ናቸው ተብሏል፡፡
ሌላኛው በየሁለት ወሩ የሚወሰደው አፐርቱድ የተሰኘው የኤችአይቪ ኤድስ መከላከያ መድሃኒትለአንድ ጊዜ ጥቅም የሚውለው መድሃኒት ዋጋ በ180 ዶላር በመሸጥ ላይ ይገኛል፡፡
የኤችአይቪ ኤድስ ቫይረስ ስርጭት በአፍሪካ ከፍተኛ ሲሆን ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን በመካከለኛው ምስራቅ፣ በምስራቅ አውሮፓ እና ደቡብ አሜሪካ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል፡፡