የሊቢያ አቃቢ ህግ የሙዓማር ጋዳፊ ልጅ ለፕሬዝዳንትነት በዕጩነት መቅረባቸውን ተቃወመ
ሌላኛው እጩ ፕሬዘዳንት ጀነራል ካሊፋ ሀፍታር ከምርጫው እንዲታገዱም አቃቢ ህግ ቢሮው ጥያቄ አቅርቧል
አቃቢ ህግ ተቃውሞውን ያቀረበው ሁለቱም እጩ ፕሬዘዳንቶች በወንጀል ይፈለጋሉ በሚል ነው
የሊቢያ ወታደራዊ አቃቢ ህግ ለፕሬዘዳንትነት በእጩነት በቀረቡት ሰይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ ላይ ተቃውሞ አቀረበ፡፡
የቀድሞ የሊቢያ መሪ ሙዓማር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ በቀጣይ ወር በሀገሪቱ በሚካሄደው ምርጫ እንደሚሳተፍ መገለጹ ይታወሳል፡፡
የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽኑ ባለስልጣን እንደገለጹት ታህሳስ 24 ቀን በሊቢያ በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እጩ በመሆን ከተመዘገቡት መካከል የቀድሞ የሊቢያ መሪ ሙአማር ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ አንዱ ነው፡፡
የሀገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል ጦር አዛዥ ካሊፋ ሃፍታር እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ አል ዲቤይባህ እና የፓርላማ አፈ ጉባዔው አጉሊያ ሳሌህ ለምርጫው ከሚወዳደሩት መካከል እንደሚገኙበትም ተጠቅሷል፡፡
የ49 ዓመቱ የጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ በሀገሪቱ ደቡባዊ ክፍል በምትገኘው ሴብሃ ከተማ ለፕሬዝዳንትንት ለመወዳደር ዕጩ ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን የሊቢያ አቃቢ ህግ ቢሮ ተቃውሞ እንዳለው ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
የሊቢያ ጠቅላይ አቃቢ ህግ ሰይፍ አል ኢስላም እና ጀነራል ካሊፋ ሀፍታር በሀገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች ሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ፈጽመዋል የሚሉ ክሶች እንደቀረበባቸው ገልጿል፡፡
ይሄንን ተከትሎም የሊቢያ ወታደራዊ ምርመራ ቢሮ ለአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን እጩዎቹ ፈጽመዋል በሚል ክስ የቀረበባቸው ጉዳዮች እስከሚጣሩ ድረስ ከፕሬዘዳናታዊ ውድድሩ በጊዜያዊነት እንዲታገዱ መጠየቃቸውን ተናግረዋል፡፡
የምርጫ ኮሚሽኑ ጥያቄውን ችላ ብሎ እጩዎቹን ከፕሬዘዳንትነት ውድድር ካላገደ ግን ለሚፈጠረው ችግር ሃላፊነቱን እንደሚወስድ የአገሪቱ አቃቢ ህግ ቢሮ አስታውቋል፡፡
ሰይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ ከአባቱ መሀማድ ጋዳፊ የስልጣን ጊዜ በፈጸማቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዓለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት እንዲሁም ጀነራል ካሊፋ ሀፍታር ደግሞ በሊቢያ ዜጎች እና ስደተኞች ላይ አሰቃቂ ወንጀሎችን ፈጽሟል በሚል ወንጀል በአሜሪካ ፍርድ ቤቶች የሚፈለጉ ሰዎች መሆናቸውንም ተቋሙ አስታውሷል፡፡
የሊቢያው የቀድሞ መሪ ሙአመር አል ጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ በፈረንጆቹ በ 2011 አባቱ በኔቶ መራሹ ተልዕኮ ከመገደላቸው በፊት ሁነኛ የሀገሪቱ ሰው እንደነበር ይገለጻል፡፡
ሊቢያ በፈረንጆቹ ከ 2011 ጀምሮ በእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች ሲሆን በፈረንጆቹ ታህሳስ 24 የሚካሄደው ምርጫ ግን ከ 10 ዓመት በኋላ ሀገሪቱን ወደ ሰላም ይመልሳል የሚል ተስፋ ተጥሎበታል፡፡ በኔቶ የተመራውና ሙአማር ጋዳፊን ከስልጣን ያስወገደው ተልዕኮ በበርካቶች እንደ ስህተት ሲወሰድ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባም ትልቅ ስህተት እንደነበር መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
የጋዳፊ ልጅ ሰይፍ አል እስላም ጋዳፊ ላለፉት 10 ዓመታት ከሊቢያ ሕዝብ ተሰውሮ መቆየቱን ከኒውዮርክ ታይምስ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ገልጾ ነበር፡፡