የሊቢያ ተፋላሚዎች የተኩስ አቁም ድርድር ያለስምምነት ተጠናቀቀ
በሩሲያ ሞስኮ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመፈራረም የተገኙት እውቅና የተሰጠው የሊቢያ ናሽናል አኮርድ መንግስት መሪ ፋይዝ አል ሲራጅና የሊቢያ ናሽናል አርሚ መሪው ጄነራል ካሊፋ ሀፍታር ትላንት ጥር 4/2012 ዓ.ም ከስምምነት ሳይደርሱ ቀርተዋል፡፡
ሁለቱ ሀይሎች ከስምምነት እንዲደርሱና በተለይ በትሪፖሊ ያለው ውጥረት እንዲረግብ ሩሲያና ቱርክ ለስምንት ሰዓታት የቆየ ድርድር አድርገዋል፡፡
በድርድሩ በተባበሩት መንግስታትና በምዕራባዊያኑ እውቅና የተሰጠው በትሪፖሊ የሚገኘው የናሽናል አኮርድ መንግስት ተኩስ ለማቆም በመስማማት ፊርማውን ያኖረ ሲሆን በተቃራኒው ጄነራል ካሊፋ ሀፍታር ሳይስማሙ ቀርተዋል፡፡
ሁለት የተለያዩ የሀይል ክንፎችን የሚመሩት የአንድ ሀገር መሪዎች ፊት ለፊት ሳይገናኙ በሩሲያና ቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች አማካኝነት ነበር ሲደራደሩ የነበረው፡፡
የቱርኩ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሜቭሉት ካቩሶክሉ ጄነራል ካሊፋ ሀፍታር ዛሬም ቢሆን ስምምነቱን እንደሚፈርሙ ግምታቸውን ቢገልፁም ለጄነራሉ ቅርበት አላቸው የተባሉ መገናኛ ብዙሃን ግን ጄነራሉ የስምምነት ፊርማ እንደማያኖሩና እንዲያውም ሞስኮን ለቀው ሳይወጡ እንዳልቀሩ ገልፀዋል፡፡
የነዳጅ ባለሀብት የሆነችው ሰሜን አፍሪካዊት ሀገር ሊቢያ በ2011 የአረብ አብዮት መሪዋን ሞሃመድ ጋዳፊን ካጣች ወዲህ መረጋጋት አልታየባትም፡፡ ያለፉት ዘጠኝ ወራት ደግሞ ዋና ከተማዋ ትሪፖሊ በተኩስ ልውውጥ የተናወጠችበት ነው፡፡
ምንጭ፡- ሲጂቲኤን