ስምምነቱን የሁለቱ ተፋላሚ ልዑካን በተባበሩት መንግስታት የጄኔቭ ቢሮ ተገኝተው ተፈራርመዋል
ስምምነቱን የሁለቱ ተፋላሚ ልዑካን በተባበሩት መንግስታት የጄኔቭ ቢሮ ተገኝተው ተፈራርመዋል
የሊቢያ ተፋላሚ ኃይሎች ዛሬ የተኩስ አቁም ስምምነት ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡
በፋይዝ አልሳራጅ የሚመራው እና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዕውቅና ያለው የሊቢያ ብሔራዊ ሸንጎ እንዲሁም በካሊፋ ሃፍታር የሚመራው የሊቢያ ብሔራዊ ጦር የተኩስ አቁም ስምምነት ለይ መድረሳቸውን ሪዩተርስ ዘግቧል፡፡
በመንግስታቱ ድርጅት የሊቢያ ጊዜያዊ ተወካይ ስቴቫኒ ዊሊያምስ የተኩስ አቁም ስምምነቱ አሁኑ እንደሚጀመር አስታወቁ፡፡ በመሆኑም ሁሉም በሊቢያ ጉዳይ ሁለቱንም ወገኖች ሲደግፉ የነበሩ የውጭ ኃይሎች ከድርጊታቸው መቆጠብ አለባቸው ብለዋል፡፡ የመንግስታቱ ድርጅት ተወካይ ይህ ስምምነት የተደረገበት የዛሬው ዕለት ለሊቢያ ሕዝብ ታላቅ ቀን ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡
ስምምነቱ የተደረገው በተባበሩት የጄኔቭ ቢሮ ሲሆን የሁለቱ ተፋላሚዎች ልዑካን ተገኝተዋል፡፡ይህንን ስምምነት ዕውን እንዲሆን ያደረገው የመንግስተቱ ድርጅት ነው ያሉት ስቴቫኒ ዊሊያምስ ይህ እርምጃ ለሊቢያ ሰላምና መረጋጋት አይነተኛ ሚና እንዳለው አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው የተኩስ አቁም ስምምነቱን የፈረሙት አካላት ለዚህ ተገዥ እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡፡ በስምምነቱ ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት ዲፕሎማቱ የሊቢያ ሕዝብ ዘላቂ ሰላም ይገባዋል ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ጉዳና ደህንነት ፖሊሲ ከፍተኛ ተወካይ ጆሴፍ ቦሬል ፎንቴለስ የሊቢያ ተፋላሚ ኃይሎች ወደ ስምምነት መምጣታቸው በሀገሪቱ የፖለቲካ ድርድር እንዲመጣ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡ የአውሮፓ ሕብረትም ይህንን ለመደገፍ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በርካቶች ይህንን የተኩስ አቁም ስምምነት በጥርጣሬ እያዩት ሲሆን በሊቢያ ጉዳይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጊዜያዊ ተወካይ ስቴቫኒ ዊሊያምስ ግን ጥርጣሬው እንዲያሸንፍ መፈቀድ የለበትም ብለዋል፡፡
በተኩስ አቁም ስምምነት የተጀመረው የፋይዝ አልሳራጅና የካሊፋ ሃፍታር ስምምነት ወደ ፖለቲካዊ ድርደር ሊያመራ ይችላል የሚለው ጉዳይ መነጋገሪያ ሆኗል፡፡