ሆላንዳዊው አርኔ ስሎት በሊቨርፑል የርገን ክሎፕን ለመተካት ተስማሙ
ሊቨርፑል ስሎትን ለማስፈረም ለፌኖርድ ከ9 ሚሊየን ዩሮ በላይ ካሳ ለመክፈል መስማማቱ ተዘግቧል
ፌኖርድ የ2022/23 የኢርዲቪዜ ዋንጫን እንዲያነሳ ያደረጉት ስሎት ወጣት ተጫዋቾችን በማብቃት ይታወቃሉ
ሊቨርፑል ሆላንዳዊውን አሰልጣኝ አርኔ ስሎት ለማስፈረም መስማማቱ ተነገረ።
የ45 አመቱ ስሎት የውድድር አመቱ እንደተጠናቀቀ ቀያዮቹን የሚሰናበቱትን ጀርመናዊ አሰልጣኝ የርገን ክሎፕ ይተካሉ።
ሊቨርፑል አሰልጣኝ ስሎትን ለማስፈረም ለፌኖርድ 9 ነጥብ 6 ሚሊየን ዶላር ካሳ ለመክፈል ያቀረበው ጥያቄ ባለፈው ሳምንት ውድቅ መደረጉ ሲዘገብ ቆይቷል።
ዘ አትሌቲክን ጨምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ግን ሁለቱ ክለቦች ስምምነት ላይ መድረሳቸውን እያስነበቡ ነው።
ቀያዮቹ ለፌኖርድ የሚከፍሉት ገንዘብ ዙሪያ የሆላንድና የእንግሊዝ መገናኛ ብዙሃን የተለያየ አሃዝ ቢያወጡም አሰልጣኝ ስሎት ቀጣዩ የሊቨርፑል አሰልጣኝ መሆናቸው ተረጋግጧል ተብሏል።
በ2021 ፌኖርድን ማሰልጠን የጀመሩት አርኔ ስሎት የ2022/23 የኤርዲቪዜ ዋንጫን አንስተዋል፤ በዚህ የውድድር አመትም ክለባቸውን ለሆላንድ ዋንጫ ያበቁ ሲሆን፥ በኤርዲቪዜው ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
አርኔ ስሎት የፕሪሚየር ሊግ ክለቦችን የማሰልጠን ፍላጎት እንዳላቸው መግለጻቸውን ተከትሎ ባለፈው አመት ስማቸው ከቶትንሃም ጋር ሲነሳ መቆየቱ ይታወሳል።
በማጥቃት ላይ የተመሰረተ ጨዋታን የሚከተሉት ስሎት ወጣት ተጫዋቾችን በፍጥነት ለትልቅ ክብር የማብቃት ችሎታቸው ሊቨርፑል የየርገን ክሎፕ ተተኪ እንዲሆኑ ማድረጉ ተጠቁሟል።
ባየር ሊቨርኩሰንን ለመጀመሪያ የቡንደስሊጋ ክብር ያበቃው የቀድሞው የሊቨርፑል አማካይ ዣቪ አሎንሶ ወደ አንፊልድ ተመልሶ ቀያዮቹን እንዲያሰለጥን ለቀረበለት ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ሳይሰጥ ቀርቷል።
የስፖርቲንግ ሊዝበኑ ሩበን አሞሪምም ሊቨርፑልን እንዲያሰለጥኑ ከታጩት መካከል እንደነበሩ ይታወሳል።
የጨዋታ መንገዳቸውም ሆነ ጸባያቸው በጀርመናዊው የርገን ክሎፕ የተወደሰላቸው ሆላንዳዊው አርኔ ስሎት ግን የቀያዮቹ የመጨረሻ ምርጫ ሆነው የውድድር አመቱ ሲጠናቀቅ ፊርማቸውን እንደሚያኖሩ ይጠበቃል።