ሃቨርትና ዋይት የደመቁበት ፤ ሰማያዊዮቹ ከ1986 ወዲህ ከባድ ሽንፈት ያስተናገዱበት የለንደን ደርቢ
በኤምሬትስ ቼልሲን ያስተናገደው አርሰናል 5 ለ 0 በሆነ ሰፊ ውጤት አሸንፎ መሪነቱን አጠናክሯል
በመርሲሳይድ ደርቢ ኤቨርተን በጉዲሰንፓርክ ሊቨርፑልን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል
አርሰናል የምዕራብ ለንደኑን ቼልሲ በሰፊ ልዩነት አሸንፎ የፕሪሚየር ሊጉን መሪነት አጠናክሯል።
በምሽቱ የኤምሬትስ ተጠባቂ ጨዋታ መድፈኞቹ 5 ለ 0 በሆነ ውጤት አሸንፈዋል።
ሊያንድሮ ትሮሳርድ በ4ኛ ደቂቃ ያስቆጠራት ግብ የሚኬል አርቴታ ቡድን የመጀመሪያውን አጋማሽ እየመራ እንዲወጣ አስችሎታል።
ቤን ዋይት ሁለተኛው አጋማሽ በተጀመረ በሰባተኛው ደቂቃ ሁለተኛዋን ጎል ካስቆጠረ በኋላ ይበልጥ የተነቃቁት መድፈኞቹ ካይ ሃቨርት በስምንት ደቂቃዎች ውስጥ ባስቆጠራቸው ሁለት ጎሎች የበላይነቱን አሳይቷል።
እንግሊዛዊው ተከላካይ ዋይት በ70ኛው ደቂቃ ለራሱ ሁለተኛዋን ለክለቡ አምስተኛውን ግብ አስቆጥሮም ጨዋታው 5 ለ 0 ተጠናቋል።
ውጤቱ በፕሪሚየር ሊጉ በአስቶንቪላ፤ በሻምፒዮንስ ሊግ የሩብ ፍጻሜ ጨዋታ ደግሞ በባየር ሙኒክ የተሸነፈው አርሰናል በፕሪሚየር ሊጉ ፉክክር ዳግም መመለሱን ያሳየ ነው ተብሏል።
ማርቲን ኦዲጋርድ ስምንት የጎል እድሎችን የፈጠረበትና የጨዋታው ኮከብ ሆኖ የተመረጠበት ጨዋታ መድፈኞቹ ፕሪሚየር ሊጉን በሶስት ነጥብ ልዩነት (77) እንዲመሩ ከማስቻሉ ባሻገር የጎል ልዩነቱንም አስፍቷል።
የማርሲዮ ፖቼቲኖ ቡድን በአንጻሩ ከ1986 ወዲህ በለንደን ደርቢ የገጠመው ከባድ ሽንፈት ሆኖ ተመዝግቧል።
በኤፍኤ ካፕ ግማሽ ፍጻሜ በማንቸስተር ሲቲ የተሸነፉት ሰማያዊዮቹ በፕሪሚየር ሊጉ ከመድፈኞቹ በ30 ነጥብ ዝቅ ብለው 9ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጠዋል።
በፕሪሚየር ሊጉ የዋንጫ ፉክክር ተጠባቂ ከሆኑ ጨዋታዎች መካከል አንዱ ዛሬ ምሽት ይደረጋል፤ የመርሲሳይድ ደርቢ።
በ74 ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ የተቀመጠው ሊቨርፑል ተስተካካይ ጨዋታውን (34ኛ ሳምንት) በጉዲሰንፓርክ ከኤቨርተን ጋር ያደርጋል።
ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎች ያሉት ማንቸስተር ሲቲ በበኩሉ ነገ ከሜዳው ውጭ ብራይተንን ይገጥማል።
የሊጉ መሪ አርሰናል የፊታችን እሁድ በሰሜን ለንደን ደርቢ ቶተንሃምን የሚገጥምበት ጨዋታም ተጠባቂ ነው።