ዝነኛ አትሌቶች የተሳተፉበት የለንደን ማራቶን
አልማዝ አያና እና ገንዘቤ ዲባባን ጨምሮ በርካታ አውቅ አትሌቶች በተሳተፉበት የሴቶች ማራቶን ሲፋን ሀሰን አሸንፋለች
በወንዶቹ ማራቶን ተጠባቂዎቹ ቀነኒሳ በቀለ እና ሞ ፋራህ አልተሳካላቸውም
የለንደን ማራቶን በዛሬው እለት ሲካሄድ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ኔዘርላንዳዊ ሲፋን ሀሰን በአስደናቂ ብቃት ተመልሳለች።
ሲፋን ውድድሩን በ2 ስአት ከ18 ነጥብ 34 ሰከንድ በማጠናቀቅ ማሸነፍ ችላለች።
መገርቱ አለሙ ደግሞ ከሲፋን በሶስት ሰከንድ ዘግይታ ሁለተኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
ኬንያዊቷ ፔርስ ጄፕቺርቺር ሶስተኛ ደረጃን ይዛ ማጠናቀቅ የቻለችበት ውድድር በርካታ የኢትዮጵያ እና ኬንያ እውቅ አትሌቶች የተሳተፉበት ነው።
የ2016 ሪዮ ኦሎምፒክ የ10 ሺህ ሜትር ሻምፒዮኗ አልማዝ አያና በ2 ስአት ከ20 ደቂቃ ከ44 ሰከንድ 7ኛ ደረጃን ይዛ አጠናቃለች።
የ1 ሺህ 500 ሜትር ፈጣን ስአት ሪከርድ የያዘችው ገንዘቤ ዲባባ በውድድሩ ከተሳተፉ ታዋቂ አትሌቶች መካከል ትገኝበታለች።
በወንዶቹ የማራቶን ውድድር ደግሞ ኬንያዊው ኬልቪን ኪፕቱም አሸንፏል።
ኪፕቱም ውድድሩን በቀዳሚነት ለማጠናቀቅ 1 ስአት ከ41 ደቂቃ ከ12 ሰከንድ ወስዶበታል።
ሌላኛው ኬንያዊ ጆፍሪ ካምወሮር እና ኢትዮጵያዊው ታምራት ቶላ ኪፕቱምንን ተከትለው ገብተዋል።
የሶስት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ቀነኒሳ በቀለ ከመሪዎቹ ቡድን ቢሆንም ድል አልቀናውም።
የአራት ጊዜ የኦሎምፒክ ሻምፒዮኑ ሞ ፋራህም የመጨረሻው ይሆናል በተባለው ውድድር 8ኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።